አረንጓዴ አሻራ የትራንስፖርት ዘርፉ በሰውና በአካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ መቀልበሻ ነው ... ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ

93

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/2012 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ በትግበራ ላይ ያለው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር የትራንስፖርት ዘርፉ በሰውና በአካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀልበስ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተገለጸ።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ከኢትዮጵያ ክፍያ  መንገዶች  ኢንተርፕራይዝና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች ጋር በአዲስ-አዳማ የፍጥነት  መንገድ  ግራና ቀኝ ችግኝ ተክለዋል።

የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብሩ ሚኒስቴሩ በ2012 ዓ.ም  የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 3 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የያዘው ዕቅድ አካል ነው ተብሏል።

ሚኒስትሯ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ችግኝ መትከል የመንገድ፣  የአቬዬሽንና  የመርከብ  ትራንስፖርት ዘርፎች በአካባቢና በሰው ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ መቀልበስ  የሚያስችል  በመሆኑ የተለየ ትርጉም ይኖረዋል።

በመሆኑም በመንገድ ግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋራጮችም ከስራቸው  ጎን ለጎን ባለፉት  ዓመታት የተተከሉና በመተከል ላይ ያሉ ችግኞችን እንዲንከባከቡ አሳስበዋል።

ባለፈው ዓመት በሚኒስቴሩ ከተተከሉ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ችግኞች 85 በመቶው መፅደቅ እንደቻለም ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ያለፈውን ዓመት ተሞክሮ በመውሰድ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ አገራዊ ንቅናቄ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ መዘጋጀቱንም ነው ወይዘሮ ዳግማዊት የገለጹት።

ተቋማዊ የችግኝ ተከላ ተሳትፎ መጎልበት የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲውን ያግዛል ያሉት ደግሞ በሚኒስቴሩ የፐብሊክ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ትልቁ ናቸው።

የአገሪቷን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ የራሱ ድርሻ እንዳለውም ገልጸዋል።

በአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ የተጀመረው የመንገድ ግራና ቀኝ አካፋዮች  ችግኝ  በመትከል የማስዋብ ተሞክሮ ወደ ድሬዳዋ-ደዋሌ እና ሞጆ-ሀዋሳ  እንደሚቀጥል  ተነግሯል።

78 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው የአዲስ-አዳማ የፍጥነት  መንገድ  አካፋይ  ቀደም ሲል  በተተከሉ  ችግኞች ውበትን ተላብሷል።

በግንባታ ላይ ያለውን የሞጆ-ሐዋሳን ጨምሮ አገልግሎት  እየሰጡ  ያሉና  ተመሳሳይ  ስራ የሚፈልጉ የድሬዳዋ-ደዋሌ እና የሞጆ-ሀዋሳ ሁለት የፍጥነት መንገዶች አሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም