የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ስራውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

6561

አዳማ፣ ሰኔ 12/ 2012 /ኢዜአ/ የአርሲ ዩኒቨርሲቲ በደን ልማትና በአካባቢው በሚታወቁ ዋና ዋና ሰብሎች ላይ የምርምር ስራውን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዑመር ሁሴን አስገነዘቡ።

አቶ ዑመር ሁሴን የዩኒቨርሲቲው የፕሮጀክቶች ግንባታ ያሉበት ደረጃ፣ የደን ልማትና አካባቢ ጥበቃ፣ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በደን ልማትና በአካባቢው በሚታወቁ ዋና ዋና ሰብሎች ላይ የምርምር ስራውን ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚገባው አስገዝበዋል።

ከአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጋር በተያያዘ በጭላሎ፣ ካካና ሆንቆሎ ተራሮች ላይ እየታየ ያለውን የደን መመናመንና ሰው ሰራሽ ችግሮች ላይ የምርምር ስራውን ማጠናከር አለበት ያሉት ሚኒስቴሩ በተለይ ዝግባ፣ ፅድና ኮሶ የመሳሳሉ  ሀገር በቀል የዛፍ ዝሪያዎች ላይ በሙሉ አቅም መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች ሳይንሳዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከናወን ሁሉም የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር ማገዝ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ይህን ማድረግ ከቻልን በጭላሎ፣ ካካና ሆንቆሎ ተራሮች ላይ እየታየ ያለው የደን መመናመን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያገግም ከማስቻል ባለፈ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በግብርና ምርት ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ መቀነስ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ  በአርሲ ዞን የሚታወቁ ዋና ዋና ሰብሎች በተለይ ስንዴና የቢራ ገብስ ላይ ዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ስራውን በስፋትና በጥልቀት ማከናወን እንደሚገባው አቶ ዑመር ሁሴን አሳስበዋል ።

ዞኑ ለመካናይዜሽን እርሻ የተመቸ ነው ያሉት አቶ ዑመር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ግብርናውን በመደገፍና በማገዝ በምግብ ራሳችን ከመቻል አልፈን የቢራ ፋብሪካዎችን ጨምሮ ለሌሎች አግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ማቅረብ እንችላለን ብለዋል።

ይህን ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው  በብቁ የሰው ሃይል ከማደራጀት ጀምሮ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በተግባር የተደገፉ መሆን አለባቸው ብለዋል ።

ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ዩኒቨርሲቲው ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራትና የጥናትና ምርምር ስራዎችን በተግባር ለመደገፍ እንዲሁም በግብርና፣በጤናና በማህበራዊ ሳይንስ እያደረገ ያለው ጥረት አመርቂ መሆኑን እንደተመለከቱ ጠቅሰዋል።

የዩኒቨርሲቲው የፕሮጀክቶች ግንባታ በተሻለ ጥራትና በተቀመጠላቸው ጊዜ እየሄዱ መሆናቸውንም ተናግረዋል ።

የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዱጉማ አዱኛ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በአካባቢና ደን ልማት፣በሰብል ልማት፣በጤና ላይ ከ60 በላይ የጥናትና ምርምር ስራዎች ማከናወኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ በአካባቢው በሚታወቁ ዋና ዋና ሰብሎች፣በሀገር በቀል የደን ልማት፣በዝዋይ ሃይቅን ጨምሮ በአካባቢው ሃይቆች ላይ የተደቀነውን የእንቦጭና የመድረቅ አደጋን ለመቀልበስ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል ።

በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ብቻ ከ60 ሺህ በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን የሀገር በቀል ዛፎች ችግኝ ለመትከል አቅደናል ብለዋል።

የጥናትና ምርምር ማእከላትን ጨምሮ የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአራት ኮሌጆች እያካሄደ  ያለው የፕሮጀክቶች ግንባታ ከ95 በመቶ በላይ መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል ።

ዩኒቨርሲቲው በደን ልማት፣ በአካባቢው ጥበቃና በሚታወቁ ዋና ዋና ሰብሎች ላይ የምርምር ስራውን ትኩረት በማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስቴርና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር በመሆን በቅጥር ጊቢው ችግኝ ተክለዋል።