በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሕጻናትን ከጥቃት ለመከላከል ትኩረት መስጠት ይገባል

56

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/2012 ( ኢዜአ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከል ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አሳሰበ።

በአዋጁ ወቅት በሕጻናት ላይ የአስገድዶ መደፈርና ጾታዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ያወሳው ኮሚሽኑ የአዋጁን አፈፃፀምና የጥቃት ተጎጂ ሕፃናት ደህንነት፣ ጥቅምና መብት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ የፍትህ ሥርዓቱን ለሕፃናት ምቹና ተደራሽ እንዳይሆን ሊያደርጉ የሚችሉ ስጋቶች መኖራቸውን በፌዴራልና በተወሰኑ ክልሎች ባደረገው ፈጣን ዳሰሳ መገንዘብ መቻሉን አስታውቋል።

ለእነዚህ ክፍተቶች መፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውን ምክረ ሀሳቦችም አመላክቷል። 

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሻ በማድረግ የፌዴራልም ሆነ የክልል ፍርድ ቤቶች በከፊል በመዘጋታቸው በህጻናትና ሴቶች ላይ ለተፈጸሙት ጥቃቶች አፋጣን ምላሽ እየተሰጠ አይደለም ብሏል። 

የጥቃት ተጎጂ ለሆኑ ሕፃናት የአንድ መስኮት የተቀናጀ ምላሽ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ማዕከላት እጅግ አስፈላጊ በመሆናቸው በወረርሽኙም ወቅት እነዚህ ማዕከላት ተጠናክረው ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ መንግስት ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም ጠቁሟል። 

በፖሊስ መምሪያዎች በሚገኙ የሴቶችና ሕፃናት ጥቃት ወንጀል ምርምራ ክፍሎችም በቂ ባለሙያዎች በተለይ ዐቃብያነ ሕግና የስነ ልቦና ባለሙያዎች ተሟልተው ባለመገኘታቸውና ሌሎች ግብረኃይሎች ድጋፋቸውን በማቆማቸው የተሟላ ሥራ እየሠሩ አለመሆኑን መገንዘቡንም ገልጿል። 

በወረርሽኙ ወቅት በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በተለይም አስገድዶ መድፈር፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋና ግርዛት ቁጥር ጨምሯል የሚሉ ሪፖርቶች ከተለያዩ ተቋማት እየተገለጹ ስለመሆኑም አውስቷል።

ይሁንና ሪፖርቱ ከወረርሽኙ በፊትና በኋላ ስላለው ሁኔታ በተገቢው መንገድ ስለመጠናቱና የተሟላ ማስረጃ ስለመኖሩ ግልጽ ባለመሆኑ ለማረጋገጥ አስቸጋሪ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አፋጣኝ ትኩረት ግን ያሻዋል ብሏል።

ለሕፃናት ምቹና ተደራሽ የፍትህ አገልግሎት የማግኘት መብትን የሚያስከብሩት የፍትህ አካላት የኮቪድ- 19ን ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚወስዷቸው እርምጃዎችና የሚወስኗቸው ውሳኔዎች የሕፃናቱን ደህንነትና ጥቅም ከሚያስጠብቁ መርሆዎች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸውም ጠቁሟል። 

በፌዴራልም ሆነ በክልል ፍርድ ቤቶች የሕፃናት ጥቃት ጉዳዮችን የሚያዩ ችሎቶች በተሟላ ኃይል እንዲሠሩም ኮሚሽኑ አመልክቷል።

የሕፃናት ጉዳይ የሕፃናቱን ነፃነት፣ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ደህንነት በተገቢው መንገድ ለመጠበቅ ሲባል በተዘጋጁ ችሎቶች ብቻ እንዲታይ፤ አስገዳጅ ሁኔታ ከተፈጠረም የጥንቃቄ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው አስገንዝቧል። 

የአንድ መስኮት የተቀናጀ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ማዕከላት በተለይ ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሕፃናት አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ለማድረግ የተቋቋሙ በመሆኑ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሰብሳቢነት የሚመራው ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ይህንኑ እንዲያረጋግጥ ጠቁሟል።

የአንድ መስኮት ማዕከላቱ ከቀድሞው በበለጠ አቅማቸውን አጠናክረው ተገቢውን አገልግሎት ለሕፃናት ተደራሽ ማድረግ ይችሉ ዘንድ እንደ ዩኒሴፍ እና በጉዳይ ላይ የሚሰሩ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ክፍሎች የፋይናንስና የቴክኒክ እገዛ ማድረግ አለባቸውም ነው ያለው።  

በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የሚመረምሩ የፖሊስ ክፍሎችም አስፈላጊ ባለሙያዎችን አሟልተው ምርመራዎችን በፍጥነት በመምራት በአፋጣኝ ለፍርድ ቤት እንዲቀርቡ እንዲያደርጉም አመልክቷል።

ሕፃናት ከጥቃትና ብዝበዛ ነፃ በሆነ ሁኔታ በመንከባከብ ለሁለንተናዊ እድገታቸው ተገቢውን ጥረት ከሚያደርግ ወላጅ ጋር የመኖር መብታቸው ሳይቋረጥ እንዲከበር የቤተሰብ ችሎቶች ከቀለብ ጉዳይ በተጨማሪ በልጅ አስተዳደግ ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ እንዲደረግም ጠይቋል። 

በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ሪፖርት ማድረጊያ ነፃ የስልክ መስመሮች በተሟላ ሁኔታ መስራታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲል የኮሚሽኑ መግለጫ አትቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም