የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን የሚያነቃቁ አዳዲስ አሰራሮችን ለመተግበር እየተሰራ ነው

218

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/2012 ( ኢዜአ) የአገር ውስጥ ቱሪዝም ልማትና የጎብኚዎችን ፍላጎት የሚያነቃቁ አሰራሮችን ለመተግበር አዲስ ስትራቴጂ ቀርጾ እየሰራ መሆኑን የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

መልክዓ ምድሯና የተፈጥሮ ሀብቶቿ ኢትዮጵያን በበርካታ ጎብኚዎች ተመራጭ ቢያደርጋትም በተቃራኒው የአገር ውስጥ ቱሪዝም ልማት እንዳልተሰራበት ይነገራል።

ለዚህ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከልም ዜጎቿ የአገራቸውን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች እንዲያውቁና እንዲጎበኙ በቂ የማስተዋወቅ ስራ አለመሰራቱ አንዱ ነው።

በመሆኑም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ሃብትና ከዘርፉም መገኘት ያለበትን ገቢ ማሳደግ የሚያስችል አዲስ ስትራቴጂ ቀርጾ እየሰራ ሲሆን ትኩረቱም የአገር ውስጥ ቱሪዝም ልማት ነው።

በሚኒስቴሩ የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ይስፋልኝ ሃብቴ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ልማት አሁናዊ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የሕዝቡን የቱሪስት መዳረሻዎች የመጎብኘት አናሳ ልምድ ለማጎልበት በባንኮችና በሌሎችም ተቋማት ጉብኝትን መሰረት ያደረገ የቁጠባ አሰራር መጀመርን ታሳቢ ያደረጉ አሰራሮችን ለመተግበር ታስቧል።

በተለያዩ አገራዊ ቋንቋዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ የማስተዋወቅ ስራም ሕዝቡ አካባቢውን ብሎም አገሩን የመጎብኘት ልምድ ማጎልበቻ ሆኖ የሚሰራበት ነው ብለዋል።

አገሪቷ በስፋት ያላትና ያልተጠቀመችበት ዘርፍ ነው በሚባለው የአርት ቱሪዝም ላይም በተመሳሳይ እንደሚሰራበት ነው አማካሪው የገለጹት።

ከከተማ የቱሪዝም መዳረሻዎች በመዲናዋ የሚገኘውን የአንድነት ፓርክ ጨምሮ ግንባታ ላይ ያሉት የእንጦጦና የሸገር ፕሮጀክቶች ሊጎበኙ የሚገባቸው እንደሆኑም ጠቁመዋል።

እነዚህንና መሰል መዳረሻዎችን በመገንባት የአገሪቷን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ለመጠቀም እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም አንስተዋል።

የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ቱሪዝም ጥምረት ጠንካራና የማይንገዳገድ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ማረጋገጥ ያስችላል ያሉት ደግሞ የሚኒስቴሩ የዓለምአቀፍ ቱሪዝም ፋሲሊቴሽን ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ናቸው።

ዓለም አቀፉን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ የጎብኚዎች ቁጥር በመቀነሱ በዘርፉ የተፈጠረውን ጫና ለመቋቋም ስትራቴጂ ተቀርጾ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም