በበጀት ዓመት መዝጊያ ወቅት የሚፈጸም ግዢ ተጠያቂነት እስከ ምን ድረስ ነው?

124

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2012(ኢዜአ) የግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ 'በተቋማት የሚፈጸም ያልታቀደ ግዢ ተቀባይነት የለውም' ሲል፤ ዋና ኦዲተር ደግሞ 'እስካሁን የኦዲት ግኝት ያለባቸውን ተቋማት ተጠያቂ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል' ብሏል።

በተለምዶ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ዓመቱ መጨረሻ ላይ በርከት ያለ ግዢ ያካሄዳሉ፤ ስሙንም 'በጀት መዝጊያ' ብለው ይጠሩታል።

በዚህ ወቅት በሚፈጸም ግዢ የተጋነነ ዋጋ እና ጥራቱን ያልጠበቀ ዕቃ መቅረቡ ደግሞ ተለምዷል።

ተቋማት የያዙት በጀት ተመላሽ እንዳይሆን በሚያደርጉት ጥረት በበጀት መዝጊያ ወቅት በሚፈጸም ግዢ የህዝብና የአገር ሃብት ለብክነት ይዳረጋል።

ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ብክነት እያስከተለ በመምጣቱ ግዢዎች በታቀደ መንገድ እንዲፈጸሙ የማዕቀፍ ግዢ መጀመሩ ይታወሳል።

የመንግስት ተቋማት በማዕቀፍ ግዢ ዘዴ እየተጠቀሙ ቢሆንም አሁንም በርካታ ያልታቀዱ ግዢዎች እየተፈጸሙ መሆኑን የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ያረጋግጣል።

በተለይ ደግሞ በዚህ ዓመት ከኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሺኝ መከሰት ጋር ተያይዞ ያልታቀዱ ግዢዎች የሚጠበቁ ቢሆንም በዓመቱ መጨረሻ ላይ የሚካሄድ ግዢ ተቀባይነት እንደማይኖረው ኤጀንሲው ገልጿል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ማርታ ሊዊጂ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከመንግስት አጠቃላይ በጀት እስከ 70 በመቶ ለግዢ የሚውል ነው።

ይህ ትልቅ ሃብት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በማድረግ ግዢዎች በማዕቀፍ እንዲፈጸሙ ቢታሰብም አመርቂ ውጤት ሊመጣ እንዳልቻለ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት መስሪያ ቤቶች ዓመቱ መጨረሻ ላይ ግዢ እንዲፈጽሙ የሚያደርግ ህግና አሰራር ባይኖርም በማዕቀፍ ግዢ መዘግየት የተነሳ ክፍተት እየተፈጠረ እንደሆነ ያመለክታሉ።

ዋና ዳይሬክተሯ መስሪያ ቤቶች ሳይታቀድ የሚፈጽሙት ግዢ ከህግ ውጪ መሆኑን በመገንዘብ ተጠያቂነት እንዳለባቸው ሊያውቁ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ግዢ መፈጸም ካለባቸው የመንግስት አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ እንዳይቆም ሊያግዙ ለሚችሉ ጉዳዮች ብቻ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በበኩሉ ከግዢና ተያያዥ የመንግስት በጀት ብክነት ጋር የሚገናኙ ጉዳዮችን በሕግ ለመጠየቅ ዝግጅት ማድረጉን ይገልጻል።

ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንደሚሉት፤ ከዓመት ወደ ዓመት መሻሻል ከማያሳየው የኦዲት ግኝት ችግሮች ለመላቀቅ ተጠያቂነትን ማጠናከር ይገባል።

ከግዢና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚታዩ የኦዲት ግኝቶችን ወደ ተጠያቂነት ለማምጣት መረጃ ተጠናቅሮ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መድረሱን አቶ ገመቹ ገልጸዋል።

በዚህ በጀት ዓመት በተለይ ዩኒቨርሲቲዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ቢታሰብም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አጋጥሞ የነበረው ችግር እንቅፋት መሆኑን አስታውሰዋል።

''የዩኒቨርሲቲዎች ችግር ሲረግብ ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሺኝ በማጋጠሙ የመንግስት ትኩረት በበሽታው ላይ እንዲሆን አድርጎታል'' ብለዋል።

እንደ አቶ ገመቹ ገለጻ፤ ባሉት የኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ ርምጃ መውሰድ ካልተቻለ ችግሩ ወደከፋ ሁኔታ ያመራል።

ለዚህ ደግሞ ምናልባት ጥፋተኛ የሆኑ ግለሰቦች ዳግም ተመሳሳይ ወደ ሆነ ስህተት እንደማይገቡ ማረጋገጥ የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በመንግስት መስሪያ ቤቶች በፋይናንስ ህጋዊነት ኦዲት ወቅት ከሚያጋጥሙት ዋና ዋና ግኝቶች መካከል አንዱ ግዢ ሲሆን ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ግዢ ተፈጽሞ እንደሚገኝ በተለያየ ወቅት ባቀረበው ሪፖርት ውስጥ ማመላከቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም