ኢትዮጵያዊያን የሕዳሴው ግድብ ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ድጋፋቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ምሁራን ተናገሩ

88

ባሕርዳር፣ ሰኔ 12/2012 ( ኢዜአ ) ኢትዮጵያዊያን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ድጋፋቸውን በአንድነት ማጠናከር እንዳለባቸው የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

ምሁራኑ በሕዳሴው ግድብ  ዙሪያ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በባሕርዳር ከተማ ተወያይተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የውኃ ምህንድስና ምሁርና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ዶክተር አሰግዶም ጋሻው እንዳሉት የግድቡ መገንባት ግብፅን በማንኛውም መንገድ የሚጎዳ አይደለም።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ የውኃን ትነት በመቀነስ ከአስዋን ግድብ በብዙ እጥፍ የተሻለና ወጪ ቆጣቢ የሆነ ዘመናዊ ግድብ ነው።


ኢትዮጰያ ግድቡን የመገንባትና የመጠቀም ሕጋዊ መብቷ በዓለም አቀፍ ሕጎች ሁሉ የተፈቀደ ቢሆንም የግብፅ ተቃራኒ እንቅስቃሴ በራስ ሀብት የመጠቀም ነፃነትን የሚጋፋ ነው።

ይህን የተቃርኖ እንቅስቃሴም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ የበለፀገችና ያደገች ሀገር እንዳትሆን ካላቸው ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ ተናግረዋል።

የግብፃውያን የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረቱ ግድቦች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመጣ በመሆኑ አሳስቧቸዋል ብለዋል።

"አሁን እየቀረቡ ያሉ ሀሳቦችና መከራከሪያዎች ለ21ኛውን ክፍለ ዘመን አይመጥኑም "ያሉት ዶክተር አስግዶም ይህም የውኃ ሀብቱን በብቸኝነት የመጠቀም የግለኝነት አባዜ የመነጨ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብፆች ተለዋዋጭ ባሕሪ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ በኩል በተሰራው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ የፖለቲካና የድርድር ሥራ የግድቡ ግንባታ አፈጻጸም አሁን 74 በመቶ ደረጃ ሊደርስ ችሏል።

አሁንም ከድርድሩ በተጓዳኝ ቀሪ ሥራዎችን ፈጥኖ በማጠናቀቅና ወደ ሥራ ማስገባት ችግሩን እንደሚቀንሰው አሰረድተዋል።

ግብፅ በተለያዩ ሀገራት ስለ ግድቡ የተሳሳቱ መረጃዎችን በመስጠት የማደናገር ሥራ እያከናወነች መሆኑን አመልክተው፤ ይህን ለመመከትም ኢትዮጵያዊያን አንድ በመሆን በተለያዩ ቋንቋዎች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መከናወን አለብን ብለዋል።


በዩኒቨርስቲው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ በበኩላቸው "የግብፅ ፖለቲከኞች የውስጥ ችግር ሲገጥማቸው የዓባይን ጉዳይ መጠቀሚያ ያደርጉታል" ሲሉ ገልጸዋል።


በአባይ ውኃ ለዘመናት በብቸኝነት መጠቀም የቅኝ ገዥ ዓይነት እሳቤ እንዲይዙ እንዳደረጋቸው ጠቅሰው፤ ሁሌም በኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነት እንዳይፈጠር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞችም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ለዚህ ጉዳይ ባለቤት ሆኖ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።


በማንኛውም የፖለቲካም ሆነ ሌላ ጉዳይ አለመግባባቶች ቢኖሩ ተነጋግሮ በመፍታት የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጰያን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ግድቡ በተያዘው አግባብ መጠናቀቅ አለበት ያሉት ፕሮፌሰሩ የዚህ ፕሮጀክት ስኬታማነት ወደፊት ለሚመጡ ተመሣሣይ ፕሮጀክቶች ጭምር ጉልበት እንደሚሆን አመልክተዋል።

በግድቡ ዙሪያ መንግሥትና ሕዝብ ከዚህ ቀደም ከነበረው ትብብር በተሻለ በጋራ በመሥራት ለፍጻሜ እንዲበቃ ድጋፋቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

"ግብፅ በኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥትና ኢኮኖሚ እንዳይኖር ለረጀም ዘመናት ስትሰራ ኖራለች" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር  ቻላቸው ታረቀኝ ናቸው።

ግብፅ በዓለም ፊት ጠንካራ የዲፕሎማሲና  ቅስቀሳ ሥራ በማከናወን በሀገሯ ውስጥም ሁሉም ዜጎቿ በአባይ ጉዳይ አንድ ዓይነት ቋንቋ ይናገራሉ ብለዋል።

"ኢትዮጵያን ለማዳከም በልዩነታቸው መግባት" የሚል ስትራቴጂ ታራምዳለች ያሉት ምሁሩ ግድቡ የልማት ብቻ ሳይሆን የብሔራዊ ኩራት፣ አንድነትና ሰላም ማስቀጠያ ምንጭ በመሆኑ በማንኛውም መንገድ አንድነትን መጠበቅ የግድ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰለጠነ ፖለቲካ መጓደልን በማስተካከል መተባበርና አንድነት አገልብቶ ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ መቆም ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያውያን የወደፊት ተስፋ የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለግብ እንዲደርስም ምሁራን፣ መንግሥት፣ ሕዝቡና በውጭ  የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም