በሦስት የሰብል ዓይነቶች ጥራትና ምርታማነትን ለማምጣት የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ተዘጋጀ

121

መቀሌ፣ ሰኔ 12 /2012 (ኢዜአ) በሦስት የሰብል ዓይነቶች ጥራትና ምርታማነት ለማመጣት የሚያግዝ የቴክኖሎጂ ሽግግር መርሀግብር መዘጋጀቱን በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የትግራይ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በጽሕፈት ቤቱ የዘር ብዜትና ሥርጭት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አብርሃም ገብረ ሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት  በ2012/13 የምርት ዘመን ለሚከናወነው ለዚሁ የቴክኖሎጂ ሥራ 63ሺህ ሔክታር መሬት ተሰናድቷል።

በዚህም በምርት ዘመኑ በመሥመር መዝራትን፣ በግብአት መጠንና አጠቃቀም እንዲሁም በዘር መዝሪያ ወቅታዊነትና ሌሎችንም የተሻሻሉ አሰራሮች በመከተል በምርታማነትና ጥራት ላይ ለውጥ ለማምጣት መሆኑን ተናግረዋል።

ምርታማነትና ጥራት እንዲመጣም የተመረጡ የሰብል ዓይነቶች ስንዴ፣ ጤፍና ሰሊጥ ናቸው።

አስተባባሪው በተያዘው የመኸር ወቅት በስንዴ ሰብል የሚሸፈን ከ31ሺህ ሔክታር መሬት መዘጋጀቱን አመልክተው በጤፍ ሰብል ደግሞ 12 ሺህ ሔክታር መሬት ይሸፈናል ብለዋል።

ቀሪው ሔክታር መሬት በሰሊጥ  የሚለማ ነው።

ለዚሁ የተዘጋጀው መሬት በአንድ አካባቢና ጎን ለጎን  የእርሻ መሬት ያላቸው 175 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች ታሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል።

ኤጀንሲው ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለአርሶ አደሮች ሥልጠና በመስጠት ለዘር ዝግጁ እንዲሆኑ መደረጉንም አስረድተዋል።

በተጠቀሰው የቴክኖለጂ ሽግግር መረሀግብር መሠረት  በአማካይ አሁን ያለውን የጤፍ ምርታማነት ከ14 ኩንታል በታች የሆነውን ከ18 ኩንታል በላይ ለማድረስ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሰሊጥ ላይ ደግሞ ጥራት ላይ መሠረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።

በማዕከላይ ዞን ታሕታይ ማይጨው ወረዳ የኮይነት ቀበሌ  አርሶአደር መንግሥተአብ ጥላሁን በሰጡት አስተያየት በተመሳሳይ ወቅትና ተመሳሳይ ዘር በአንድ በመደራጀታቸው የግብአት አቅርቦት በአንድ ቀን እንዲቀርብላቸው ማስቻሉን ተናግረዋል።

አርሶአደሩ እንዳሉት 60 አርሶአደሮች በመርሀግብሩ ታቅፈው በጋራ በመሆን 15 ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ ጤፍ ለማልማት ተዘጋጅተዋል።

ይህም ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ ትራክተርና የፀረ አረም አቅርቦቶች በአንድ ላይ መጠቀም እንዲችል የሚረዳቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ተደራጅተው አንድ ላይ ተመሳሳይ የሰብል ዘር መዝራት ጠቀሜታ እንዳለው ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ግንዛቤ በመረሃ ግብሩ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የደቡባዊ ዞን እንዳመሆኒ ወረዳ የዓይባ ቀበሌ አርሶ አደር ርዕሰደብሪ ሚካኤል ዮሐንስ ናቸው።

አሰራሩ ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምር እንደሚያደርግ መረዳታቸውን አመልክተዋል።

በክልሉ ደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ዞኖች የሰንዴ፣ ማዕከላይ ዞን የጤፍ እንዲሁም ሰሜን ምዕራብና ምዕራባዊ ዞኖች ደግሞ ለሰሊጥ ሰብል ተብለው የተለዩ መሆናቸውን  ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም