ንሥር ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ኮሮናን ለመከላከል ዲጂታል መሣሪያዎች ድጋፍ አደረገ

120

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) የንሥር ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የዲጂታል የሙቀት መለኪያ መሣሪያዎችን ለጤና ሚኒስቴር ድጋፍ አደረገ።

ተቋሙ ለሚኒስቴሩ የለገሳቸው አጠቃላይ ዋጋቸው ከ500ሺህ ብር በላይ የሆኑ አራት ዲጂታል መሣሪያዎችን ነው።

ድጋፉን የተቋሙ ዋና ሥራአስፈጻሚ ዳዊት ዋቅጋሪ ለጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ዛሬ አስረክበዋል።

መሣሪያው የራሱ ካሜራ፣ ዲጂታል የሰውነት ሙቀት መለኪያ፣ አውቶማቲክ የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር ማስቀመጫ አለው።

ጎን ለጎንም አውቶማቲክ የእጅ ማድረቂያ፣ ሶፍት ማስቀመጫ፣ በምስልና በድምዕ መልዕክት ማስተላለፊያ እንዲሁም የኢንተርኔት ገመዶች መቀበያ (መሰኪያ) እንደተዘጋጀለት ተጠቁሟል።

መሣሪያው ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት ያላቸውን በካሜራ አንስቶ ስለሚያስቀር የሕክምና ክትትል ለማድረግ አስተዋጽኦ አለው ተብሏል።

በተለይም ማየትና መስማት የተሳናቸው ግለሰቦች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቁ በጽሑፍና በድምፅ መልዕክት ማስተላለፍ እንደሚያስችል ተገልጿል።  

ዶክተር ደረጀ በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ ድጋፉ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ''በእጅጉ ያግዛል'' ብለዋል።

በተለይም መሣሪያው በዘመናዊ መልኩ መዘጋጀቱ ቫይረሱን ሣይንሳዊ በሆነና በቀላሉ ለመከላከል አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል። ''ፈጠራ በጣም አስፈላጊ ነው'' ሲሉም ተናግረዋል።

እንዲህ ያሉ ከንክኪ ነፃ የሆኑ መሣሪያዎች ቫይረሱን ለመከላከል አስተዋጽኦ ስላላቸው የሚመለከታቸው አካላት ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ተቋማትና ግለሰቦች ቫይረሱን ለመከላከል ያደረጉትን ድጋፍ ሚኒስትር ዴኤታው አድንቀው፤ ድጋፉ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም