በአማራ ክልል በድህረ ኮሮና የምግብ እህል አቅርቦት እንዳይፈጠር እየተሰራ ነው

53

ባሕርዳር፣ ሰኔ12/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በየጊዜው የሚከሰተውን የአንበጣ መንጋ በመከላከል ድኅረ ኮሮና የምግብ እህል አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እየሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አለባቸው ዓሊጋዝ ለኢዜአ እንደገለጹት በተለይም በምሥራቅ አማራ የአንበጣ መንጋ በበጀት ዓመቱ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ይገኛል።

በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ወሎና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳድር ዞን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የተከሰተው የአንበጣ መንጋው በሰብል ላይ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱን አውስተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሰሜን ሽዋ ዞን ጣርማበር፣ አሳግርት፣ አንኮበርና ምንጃር ወረዳዎች ላይ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በኬሚካል ርጭትና በሰው ጉልበት ማጥፋት መቻሉን ገልጸዋል።

የአንበጣ መንጋ የተከሰተበት ከ140 ሔክታር በላይ መሬት አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ በመቻሉ ድኅረ ኮሮና የምግብ እጥረት እንዳይፈጠር ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የአንበጣው መንጋው በሌሎች አካባቢዎች በመከሰት በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የግብርና ቢሮው 2 ሺህ 400 ሊትር ኬሚካል በመጠባበቂያነት መያዙን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሩ የቅድመ አሰሳ ሥራ በማከናወን የአንበጣ መንጋው ተከስቶ ካገኘው ጅራፍንና የተለያዩ ባህላዊ መንገዶችን በመጠቀም እንዲከላከል የግንዛቤ መፍጠር ሥራ ተከናውኗል።

ከመከላከል ሥራው ጎን ለጎንም ፈጥኖ በአካባቢው ለሚገኝ የግብርና ባለሙያ ሪፖርት በማድረግ የመከላከል ሥራው ፈጣን፣ ውጤታማና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

አሁን ያለውን የአንበጣ መንጋ የመከሰት ባህሪ መሠረት በማድረግም የአውሮፕላን ርጭት በሚያስፈልግበት ጊዜ ፈጥኖ መከወን አንዲቻል ከፌዴራል መንግሥት ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል።

በሰሜን ሽዋ ዞን የአንኮበር ወረዳ የዘንቦ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሀመድ ይማም እንደገለጹት በግንቦት በበቆሎ ሰብል የሸፈኑት ግማሽ ሔክታር ማሣ ሰሞኑን በተከሰተ የአንበጣ መንጋ ወድሞባቸዋል።

የአንበጣ መንጋውን ጅራፍ በማጮኽ፣ ብረት ምጣድ በማንኳኳትና ሌሎች ባህላዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ለመከላከል ቢሞክሩም ከአቅም በላይ ሆኖ የዘሩትን የበቆሎ ሰብል ማውደሙን ተናግረዋል።

በዚህም በመጪው መኸር ለማግኘት ያቀዱት ከ20 ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርት መስተጓጉሉን ጠቁመው መንግሥት ተከሰተ ተብሎ ሲነገረው በፍጥነት በመድረስ የሰብል ውድመትን እንዲከላከል ጠይቀዋል።

ባለፈው ክረምት በግማሽ ሔክታር ማሣ ላይ በቆሎ ዘርተው ከግማሽ በላይ የሚሆነው በአንበጣ መንጋ እንደወደመባቸው የገለጹት ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን የአርጎባ ወረዳ ቀበሌ 06 ነዋሪ አርሶ አደር አህመድ ዘይኑ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም የአንበጣ መንጋው አልፎ አልፎ እየተከሰተ በመሆኑ በአርሶ አደሩ ላይ ተፅዕኖ ከመፍጠሩ በፊት መንግሥት ፈጥኖ እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል።

በክልሉ በተያዘው የመኽር አዝመራ ከአራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን ከ120 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም