ለሁለት ወራት ያህል በ15 ከተሞች አጋጥሞ የነበረው የመብራት መቆራረጥ ችግር ሙሉ በሙሉ ተፈታ

53

ማይጨው፣ ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) አላማጣ ላይ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፍያ ትራንስፎርመር በመበላሸቱ ለሁለት ወራት ያህል መብራት አጥተው የቆዩ 15 ከተሞች መፍትሔ ማግኘታቸው ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰሜን ሪጅን መብራት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ገብረእግዝአብሔር ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ችግሩ አላማጣ ላይ የነበረው ባለ 24 ሜጋ ዋት የሀይል ማስተላለፍያ ትራንስፎርመር በመቃጠሉ ነው ብለዋል።

በዚህም  በትግራይና አማራ ክልል የሚገኙ 15  ከተሞች የኃይል እጥረት ችግር አጋጥሟቸው መቆየቱን ተናግረዋል።

ችግሩን በጊዚያዊነት ባለ 12 ሜጋ ዋት ትራንስፎርመር በመትከል በፈረቃ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው አሁን ሌላ ተጨማሪ ባለ 12 ሜጋ ዋት የኃይል ማስተላለፊያ ትራንስፎርመር በመተከሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ወደ ነበረበት የ24 አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ መመለሱን ገልጸዋል።

አላማጣ፣ ማይጨው ሰቆጣና ላሊበላን  ጨምሮ 15 ከተሞች የ24 የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በማይጨው ከተማ በፀጉር ማስተካከል ሥራ የተሰማረው ወጣት ሀብታሙ መሓሪ በሰጠው አስተያየት የኤሌክትሪክ ኃይል  አቅርቦት ችግር መፈታቱ በሥራው ላይ አጋጥሞት የነበረው ጫና እንዳስቀረለት ተናግሯል።

ለሁለት ወራት ያህል በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ለኪሣራ ተዳርገን ነበር አሁን ግን ዘላቂ መፍትሔ በመግኘቱ ተደስቻለሁ ያለው ደግሞ በብረታ ብርት ሥራ የተሰማራው ወጣት አማኑኤል ዳርጎ ነው።

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደዚህ ዓይነት ችግር ሲያጋጥም ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበት አሰራር ቢከተል እያጋጠመ ያለውን ችግር እንደሚቀርፍ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል።

በ15ቱ ከተሞች የመብራት መቆራረጥ ችግር ማጋጠሙን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቦ እንደነበር ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም