በአማራ ክልል 155 ሺህ ሄክታር መሬት ባለሃብቶች እያለሙ ነው

51

ባህርዳር፣ ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በዘንድሮው የመኽር አዝመራ 155 ሺህ ሄክታር መሬት በእርሻ ኢንቨስትመንት በተሰማሩ ባለሃብቶች በተለያዩ ሰብሎች የማልማት እንቅስቃሴ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የገጠር መሬት ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት የእርሻ ኢንቨስትመንቱ እየተከናወነ ያለው በዘርፉ በተሰማሩ 1 ሺህ 366 ባለሃብቶች አማካኝነት ነው።

በባለሃብቶቹ የሚለማው መሬት በአብዛኛው ለኤክስፖርት አቅርቦትና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የሰሊጥ፣ ጥጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሽላ፣ በቆሎና ሌሎች ሰብሎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ባለሃብቶች ለአካባቢው አርሶ አደሮች የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሊያመጣ በሚችል መልኩ እንዲያለሙ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የእርሻ ኢንቨስትመንት ልማቱ የአረምና የአጨዳ ወቅትን ጨምሮ በየዓመቱ ለ339 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል ።

በእርሻ ኢንቨትስመንት ቦታዎች በጉልበት ስራ የሚሰማሩ ሰራተኞች ከኮሮና ቫይረስ ራሳቸውን እንዲጠብቁ የንፅህና መጠበቂያና የማደሪያ ቦታዎችን ባለሃብቶች እንዲያሟሉ ቢሮው ከአጋር ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ በበኩላቸው ባለሃብቶች የተረከቡትን መሬት ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው እንዲያለሙ ክትትል እየተደረገ ይገኛል።

ባለሃብቶች ለአርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሊያመጣ በሚችል መልኩ የተሻሻሉ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የግብርና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።  

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግም የማዳበሪያ ግብዓትና የተሻሻሉ አሰራሮችን በምክረ ሃሳቡ መሰረት እንዲጠቀሙም ቢሮው ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በተረከቡት ሁለት ሺህ ሄክታር መሬት ሰሊጥን ጨምሮ በተለያዩ ሰብሎች በዘር እየሸፈኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ በደለሎ ቁጥር1 የዮኒና ዳኒ የእርሻ ልማት ስራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ አብርሃ ናቸው።

በእርሻ ልማቱ በጉልበት ስራ ለሚሰማሩ ከሦስት ሺህ በላይ ሰራተኞች ከኮሮናና ሌሎች ወረርሽኞች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ከመጠለያ ጀምሮ ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የምርት ማሳደጊያ ግብዓትን በመጠቀም በተለያዩ ሰብሎች ከሚያለሙት ሰብል በቀጣይ ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

በወረዳው ደለሎ ቁጥር 2 እርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ይበልጣል አሰፋ በበኩላቸው 210 ሄክታር መሬት በጥጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሽላና ሰሊጥ ሰብሎችን የማልማት ስራ እያከናወኑ ነው።

በክልሉ በዚህ ዓመት በተለያየ ምክንያት ከሰብል ልማት ውጪ የነበረ 90 ሺህ ሄክታር መሬት ወደ ልማት እንዲገባ መደረጉን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም