የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በየትኛውም ውጫዊ ተፅዕኖ እንዲስተጓጎል አንፈቅድም.. የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

72

ሆሳዕና፣ ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ተፈጥሮአዊ መብቷን በመጠቀም የአባይን ወንዝ ለኃይል ማመንጨት አገልግሎት ለማዋል የጀመረችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በየትኛውም ውጫዊ አካል እንዲስተጓጎል አንፈቅድም ሲሉ የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለፁ።

የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተመስገን ቶማስ ለኢዜአ እንደገለፁት የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በሀገሪቱ ፈጣንና ሁለንተናዊ እድገት ለማስመዝገብ  የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። 

በመሆኑም ሀገሪቱ የልማት ህልሟን ለማሳካት እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ በየትኛውም ውጫዊ ተፅዕኖ እንዲስተጓጎል መፍቀድ የለብንም ብለዋል። 

የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ተፅዕኖ ለመፍጠር ይሞከር እንደ ነበር አስታውሰው አሁንም ግድቡ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ እየተሰማ ያለው ማንገራገር ቦታ ሊሰጠው እንደማይገባ ተናግረዋል። 

ይልቁንስ ለግንባታው ዳር መድረስ የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከር ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

መንግሥትም የጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ ድርድር ብስለት በተሞላበት መልኩ በማስኬድ የግድቡን ፍፃሜ ማፋጠን እንደሚገባው ዶክተር ተመስገን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጸደቀ ላምቦሬ በበኩላቸው ሃገሪቱ የተፈጥሮ ሀብቷን በመጠቀም ልማቷን ማፋጠን እንዳትችል የሚያግዳት አንዳችም ሃይል ሊኖር አይችልም ብለዋል። 

ግድቡን ማጠናቀቅ የሃገሪቱ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን ወዳጅም ጠላትም ሊያውቀው እንደሚገባ ገልጸው ለዚህም ህዝባችን እንደማይደራደር ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።  

በተለይ ለግድቡ ፍፃሜ የሚሰስት መቀነትና ወደ ኋላ የሚመለከት እካል እንደማይኖር ዶክተር ጸደቀ ገልፀዋል።

 አስተማማኝና ዘላቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨትና ልማታችንን ለማፋጠን ግድቡ የሚያበረክተው ጠቀሜታ የጎላ ከመሆኑም ባሻገር በተፈጥሮ ደን ላይ የሚያደርሰውን ውድመት ለማስቀረት ይረዳል።

 ኢትዮጵያ የተፋሰሱን ተጠቃሚ ሀገራት ሳትጎዳ ግድቡን በመስራት ለጋራ ተጠቃሚነት እንዲውል ያሳየችው ተነሳሽነት ሊደገፍ እንጂ ተቃውሞ ሊገጥመው አይገባም ነበር ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የተግባር ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅር አዲስ ጁማአ ናቸው። 

በግድቡ መጠናቀቅ ዙሪያ በየትኛውም ውጫዊ አካል የሚንፀባረቅ ተፅዕኖ ሀገሪቱ ባላት ተፈጥሯዊ ሀብት የመጠቀም መብቷን ሊያግዳት አይችልም ብለዋል። 

ግድቡ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት መጀመር ሀገሪቱ የራሷን አቅም በማጎልበት  ተጠቃሚነቷን የምታረጋግጥበት  ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጉጉት የሚጠብቀው ጉዳይ አንደሆነም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ከቀድሞ በተሻለ እጅ ለእጅ ተያይዞ ግድቡን ከዳር ለማድረስ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሙሉ እምነት እንዳላቸው ምሁራኑ በአፅንዖት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም