የመዲናዋን የቱሪዝም መስህብነት ለማሳደግ የማልማት ሥራ እየተሰራ ነው

148

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2012(ኢዜአ) የአዲስ አበባን የቱሪዝም መስህብነትን ለማሳደግ የማልማት ሥራ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የአገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ሣሙኤል ሠይፉ ለኢዜአ እንደገለጹት የቱሪዝም መስህቦችን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመለየት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ለአገር ውስጥ ቱሪዝም ብዙ ትኩረት አልነበረም ያሉት አቶ ሣሙኤል በአሁኑ ወቅት ቱሪዝም ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ለዚህም ለአገር ውስጥ ቱሪዝም የቱሪዝም ልማት መዳረሻዎችና የአገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፊያ ቡድኖች ተደራጅተዋል ብለዋል።

አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ የቱሪዝም መስህብ መዳረሻዎች ያሏት በመሆኑ ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆኑ የመሠረተ ልማት መስፋፋትና ዕድሳት እንደሚያስፈልጋቸው አቶ ሣሙኤል ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ አብዛኛዎቹ የቱሪስት መስህቦች ያረጁ በመሆኑ ሐውልቶችና ሙዚየሞች ለተመልካች ሳቢ እንዲሆኑ ዕድሳት እንደተደረገላቸውም አመልክተዋል።

በቢሮው የቱሪስት መዳረሻ ባለሙያ አቶ አበበ አራጋው በበኩላቸው በአዲስ አበባ ጎብኚ ያልነበራቸውን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ጎልተው እንዲወጡና የሰዎችን እይታ እንዲስቡ እያደረጉ እንደሆነ አስታውቀዋል።

አቶ አበበ አያይዘውም በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት ሥራዎች በተወሰነ መልኩ ተገቱ እንጂ ብሮሸሮችን እያሰራጨን እንዲጎበኙ የማድረግ ሥራ እየሰራን ነው ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ተጀምሮ ያልተሳካውና ዘንድሮም ያልቀጠለው በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ የቱሪዝም መስህቦችን ማስተዋወቅ መሆኑን የአገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፊያ ቡድን መሪው አቶ ሣሙኤል ገልጸዋል።  

አቶ ሣሙኤል አያይዘውም ቀጣይ በዓለም አቀፍ ፣ በአገር ውስጥ በኤሌትሮኒክስና በሕትመት ሚዲያዎች የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል ብለዋል።

የእንጦጦ፣ የአንድነትና፣ የሸገር ፓርኮችን በተመለከተ አስቀድመው ግንኙነት መጀመራቸውን ገልጸው የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።  

ለከተማው ነዋሪዎች በከተማዋ ውስጥ ስላሉ የቱሪስት መዳረሻዎች በኤፍኤም 96.3 ሣምንታዊ ፕሮግራም ላይ የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በአዲስ ቴሌቪዥንም በቱሪዝም ላይ የሚሰራ ፕሮግራም መጀመሩንም አቶ ሣሙኤል አስረድተዋል።

አዲስ አበባ የበርካታ አብያተ ክርስቲያናት፣ ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶችና ሕንፃዎች፣ ሐውልቶች ያሉባት ከተማ ብትሆንም በርካታ ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ መስህቦች ያለሙ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

አዲስ አበባና በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊጎበኙ የሚችሉ የቱሪዝም መስኮች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን የቱሪዝም መስህቦች መልማት አለባቸው ብለዋል።

በቀጣይ ዓመት የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ሰፋ ባለመልኩ ለመግባት ጥናት እያደረጉ መሆናቸውን የቱሪስት መዳረሻ ባለሙያው አቶ አበበ ጠቁመዋል።

የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ከፀጥታና የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር የሚጎድላቸውን እንዲሟሉ ለማድረግ በጥናት እያስደገፉ እየሰሩ መሆናቸውን አቶ አበበ ጨምረው ገልጸዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም