መንግስት በውዝፍ ግብር ዕዳ የወሰደው የግብር እዳ ምህረትና ማቅለያ እፎይታ እንደፈጠረላቸው ባለሃብቶች ገለጹ

136

መቐለ፣  ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) መንግስት በኮሮና ምክንያት ለግብር ከፋዮች ያደረገውን የውዝፍ ግብር ዕዳ ምህረትና ማቅለያ ስራቸውን ተረጋግተው እንዲያከናውኑ እንዳስቻላቸው ባለሃብቶች ገለጹ።

በኮንስትራክሽን የስራ ተቋራጭነት ተሰማርቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ኤ ስ ኤኤ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ተቋም ስራአስኪያጅ አቶ አስመሮም መሐሪ በሰጡት አስተያየት የፌደራል መንግስት ለግብር ከፋዮች በሰጠው የእዳ ምህረትና ማቅለያ ተጠቃሚ ሆነዋል ።

የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ በታየው የስራ መቀዛቀዝ ሰራተኞች ለመቀነስና ስራችንን ለማቋረጥ አስበን ነበር ብለዋል።

 መንግስት ባደረገልን የ1ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የግብር ቅነሳ ምክንያት እንደ አዲስ ለስራ ተነቃቅተናል ያሉት አቶ አስመሮም፣ በተደረገው ምህረት እፎይታ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

በወጣው የምህረትና የእዳ ማቅለያ መመሪያ መሰረትም  ወደ ስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የህንፃ መሳሪያዎች ንግድ ስራ ባለቤት የሆኑት አቶ ተስፋይ ገብረገርግስ በበኩላቸው በኮሮና ምክንያት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የንግድ እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙ የእለት ገቢያቸው መቀነሱን ገልፀው መንግስት ችግሩን ተገንዝቦ የግብር እዳ ቅነሳ እና ማቅለያ ማድረጉ እንዲረጋጉና በአዲስ መንፈስ ለስራ እንዲነቃቁ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

የሚጠበቅብኝን እዳ ሰርቼ በተራዘመ ጊዜ እንድከፍል መደረጉ ተገቢና የተቀዛቀዘውን የንግድ ስራ የሚያበረታታ እንደሚሆንም እምነታቸውን ገልጸዋል።

በዓመት መክፈል የሚገባቸው 400 ሺህ ብር ግብር በተራዘመ ጊዜና ያለ ምንም ቅጣት እንዲከፍሉ ሁኔታዎች በመመቻቸቱ በስራየ ላይ መረጋጋት እንዲኖር አድርጓል ብለዋል።

 በኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር የመቀሌ ቅርንጫፍ ስራአስኪያጅ አቶ ተኽላይ አብርሃ እንደገለጹት በኮቪድ-19 ምክንያት የፌደራል መንግስት የንግድ እንቅስቃሴው እንዳይዳከምና ኢኮኖሚውን እንዳይጎዳ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውሰዋል።

በዚሁ መሰረት 315 ግብር ከፋዮች በቅጣትና ወለድ ምክንያት ተወስኖ የነበረውን ከ454 ሚሊዮን ብር በላይ ምህረት እንደተደረገላቸው አስረድተዋል።

በትግራይ ክልል በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ስር 1 ሺህ 600 ግብር ከፋይ ባለሃብቶች እንደሚገኙ ስራአስኪያጁ ጨምረው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በ2012 በጀት ዓመት 11 ወራት ውስጥ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ከስራአስኪያጁ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም