የቱሪዝም ዘርፉ ጉዳት ለመቀነስ በሃገር ውስጥ ቱሪስት ትኩረት ይደረጋል

3363

ጎንደር፣  ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ)  የኮሮና ወረርሽኝ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ የፈጠረውን ተፅእኖ ለመቋቋም ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳው አስታወቁ፡፡

የጎንደር ከተማን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት በሚቻልበት ሁኔታ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ምክክር ትናንት በጎንደር ከተማ ተካሄዷል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በምክክር መድረኩ ላይ እንዳሉት የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ገቢ አስተማማኝ ለማድረግ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ማጠናከር ይገባል፡፡

በአብዛኛው በውጪ ሀገር ቱሪስቶች ላይ ጥገኛ የሆነው የሀገሪቱ የቱሪዝም ገቢ በሌሎች አማራጮች በማስፋት ቀጣይነቱንና ዘላቂነቱን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የሀገር ውስጥ የቱሪዝም ስትራቴጂ ጥናት በማጠናቀቅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ስራ ላይ እንዲውል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ስትራቴጂው በተጨማሪም ከጎረቤት የአፍሪካ ሀገራት ጋር የቅርብ ትስስር በመፍጠር ቱሪስቶች ወደ ሀገራችን ለጉብኝት የሚመጡበትን ስርአት ለመዘርጋት እገዛ እንደሚኖረው ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ በቱሪዝም ዘርፉ ያስከተለውን ተጽእኖ በመቋቋም በኩል በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችና በሆቴልና ቱሪዝም የተሰማሩ አካላትን ለመደገፍ የሚያስችል የብድር ድጋፍ የሚያገኙበት አሰራር እየተመቻቸ ነው፡፡

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም በበኩላቸው ወረርሽኙ በከተማው በቱሪዝም፣ በንግድና በሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡

አሁን ላይ ከተማው ወደ ቀደመ ሰላሙ ተመልሶ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው መነቃቃት በጀመረበት ወቅት ወረርሽኙ ጫና በማሳደሩ የፌደራልና የክልል መንግስታት ሁለንተናዊ እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ በበኩላቸው ወረርሽኙ በፈጠረው ጫና በከተማው በሆቴል አገልግሎት፣ በአስጎብኝነት፣ በጉዞ ወኪልነትና በሌሎች የቱሪዝም ዘርፎች የተሰማሩ ማህበራትና ድርጅቶች ለችግር ተጋልጠዋል፡፡

በመጀመሪያው ስድስት ወራቶች ከ340 ሺህ በላይ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ከተማዋን ጎብኝተው እንደነበር ያስታወሱት ሃላፊው በሁለተኛው ስድስት ወራት ግን የቱሪስት ፍሰቱ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መቋረጡን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በቱሪዝም ዘርፉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳታፊና ተጠቃሚ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከተማ አስተዳደሩ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

በቱሪዝሙ መቀዛቀዝ ክፉኛ የተጎዱትን የዘርፉን ባለሙያዎች በመደገፍ በኩል መምሪያው በጥናት ላይ የተመሰረተ ፕሮጀክት ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የፋይናንስ ተቋማት የብድር አገልግሎት በማመቻቸት የቱሪዝም ዘርፉን ቀጣይነት በማረጋገጥ ሒደት የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጎንደር ዲስትሪክት የብድር ክፍል ሃላፊ አቶ ምስጋናው ዘሪሁን በበኩላቸው ባንኩ በቱሪዝም ዘርፉ ወረርሽኙ ያደረሰውን ተጽኖ መቋቋም እንዲቻል 14 ለሚደርሱ ሆቴሎች 100 ሚሊዮን ብር ብድር መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

አነስተኛ ወለድና የስድስት ወራት የብድር መክፈያ የእፎይታ ጊዜ ያለው 840 ሚሊዮን ብር የብድር ገንዘብ በከተማውና አካባቢው በቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ ተቋማት ለማበደር ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የከተማውን አመራሮችን ጨምሮ አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማትና ቱሪዝሙን በመደገፍ በኩል አጋዥ ናቸው የተባሉ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም