የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ለመግታት የቻይና- አፍሪካ ትብብር የማይተካ ሚና አለው

116

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12 /2012 (ኢዜአ) የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ለመግታት የቻይና አፍሪካ ትብብር የማይተካ ሚና እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።

አቶ ገዱ አስተያየቸውን የገለጹት ኮቪድ -19 ወረርሽኝን ለመግታት በተካሄደው ዓለም አቀፍ ''የአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ ኢኒሼቴቭ " የቪዲዮ ኮንፈረንስ ላይ ነው።

የዓለም ስጋት የሆነውን የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ለመግታት በቻይናና በአፍሪካ መካከል የሚደረገው ትብብር ወሳኝ መሆኑን መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ቻይና የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ለመግታት የተከተለችውን ስትራቴጂና የተገኘውን ውጤትም ሚኒስትሩ አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ለመግታት እያደረገች ባለው እንቅስቃሴ የቻይና መንግሥትና እንደ ጃክ ማ የመሳሰሉት የቻይና ባለሀብቶች እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያላቸውን እምነትም አቶ ገዱ ገልጸዋል።

ኮንፈረንሱ የኮቪድ- 19 ወረረሽኝ በታዳጊ አገሮች ኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ የሚቋቋሙበት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኮንፈረንሱን የመሩት የቻይና ስቴት ካውንስልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጨምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ኮንፈረንሱ ከመጀመሩ በፊት የቻይና መንግሥት የኮንፈረንሱን ዓላማና ጠቀሜታ በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም ''የአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ ኢኒሼቲቭ'' ዓለም አቀፍ ትብብርን ማሳደግ የኮቪድ -19 ወረርሽኝን ለመግታት የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ተብራርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም