ኢትዮጵያ ከ3 ቀናት በኋላ በሚከሰተው ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ ከጎብኚዎች ታገኝ የነበረውን ገቢ በኮቪድ-19 ሳቢያ ታጣለች

69

ኢትዮጵያ ከሶስት ቀናት በኋላ በሚከሰተው ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ ከጎብኚዎች ልታገኝ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረረሽኝ የተነሳ የምታጣ መሆኑን የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

የፊታችን እሁድ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚከሰተው ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ በአገር አቀፍ ደረጃ በላልይበላ በተለያዩ ስነስርዓቶች ይካሄዳል።

 የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ጋር በመሆን በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዶክትር ሰለሞን በላይ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የስፔስ ቱሪዝም በዓለም ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚያመነጭ ዘርፍ ነው።

የዘንድሮው ክስተት በሕይወት ዘመናችን ከሚያጋጥሙን አስደማሚ ተፈጥሯዊ እድል እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በስርዓተ ፀሐይ ውስጥ በከዋክብትና ፕላኔቶች እንቅስቃሴ ከሚፈጠሩ ክስተቶች አንዱ የሆነው ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ ጨረቃ ፀሐይን ሙሉ በሙሉ መሸፈን ሳትችል ቀለበት ሰርታ የምትታይበት ቅጽበት ነው።

በኢትዮጵያ የሚከሰተው ሙሉ ወይም ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ከጥዋቱ 12፡50 እስከ 3፡30 ቆይታ ይኖረዋል።

ግርዶሹ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐፕሊክ ጀምሮ ሱዳንን፣ ኢትዮጵያን፣ የመን፣ ኦማን፣ ፓኪስታን፣ ታይዋን፣ ህንድና ቻይናን አቋርጦ ፓስፊክ ውቅያኖስ የሚያበቃ ሲሆን ከጥዋቱ 12 ሰዓት ከ45 ደቂቃ እስከ ቀኑ 6 ሰዓት ይጠናቃቃል።

ግርዶሹ ከሚከሰትባቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለእይታ ተስማሚ እንደሆነች በስነ ፈለክ ተመራማሪዎች በመረጋገጡ በኢንስቲትዩቱ ደረጃ ብቻ ከ20 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ተመዝግበው እንደነበር አስታውሰዋል።

በተለይም በክስተቱ 90 በመቶ ጨለማ ይኖራቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ስፍራዎች መካከል ታሪካዊው የላልይበላ መካነ ቅርስ አንዱ በመሆኑ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ተጠብቆ ነበር።

ነገር ግን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱ በበርካታ አገሮች የጉዞ ዕገዳ በመጣሉ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው ጉዞ ተገትቷል።

''ያም ሆኖ በላልይበላ ከፍተኛውን የእይታ ድርሻ መያዙ፣ ታሪካዊ ስፍራ መሆኑ፣ በስፍራው የሚገኘው አቡነ ዮሴፍ ተራራም የስነ ፈለክ ምርምር ማዕከል እንዲሆን በመወሰኑ በአገር አቀፍ ደረጃ በስፍራው ሁነቱ ይከበራል'' ብለዋል።

ወደ ላልይበላ ለመሄድ ፍላጎት የነበራቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም ለህብረተሰብ ጤና ሲባል እንዳልተፈቀደ ዶክተር ሰለሞን ገልጸዋል።

በሚኒስቴሩ የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ይስፋልኝ ሀብቴ በበኩላቸው ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ክስተቱን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የማስተዋወቅ ስራ ሲከናውን መቆየቱን አውስተዋል።

ሁነቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን ለማስተናገድ አቅም ያለው ታሪካዊ የቱሪዝም አካል እንደሆነ ገልጸው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ከአንድ ሰው ብቻ በቀን በአማካይ ከ450 ዶላር በላይ ልታገኝ ትችል እንደነበር ገልጸዋል።

ነገር ግን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ኢትዮጵያ እንደምታጣ ገልጸዋል።

በላልይበላ ለሚደረገው ክብረ በዓልም የኢትዮጵያ አገር በቀል የስነ ፈለክ እውቀቶችንና ከፍተኛ ጎብኝዎችን የሚያስተናግደውን ላልይበላን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጠር ገልጸዋል።

በላልይበላ የሚደረገው አከባበር በርካታ አህጉርና ዓለም አቀፍ የስነ ፈለክ ተቋማት እንዳሉበትና በቴሌቪዥንና በማህበራዊ ሚዲያዎች የቀጥታ ስርጭት እንደሚኖረው ተገልጿል።

ክስተቱ በቴሌስኮፕ ተቀርጾ ለትውልድ የሚተላለፍና ለጥናትና ምርምርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ዶክተር ሰለሞን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሚታየው የፀሐይ ግርዶሽ ከ86 እስከ 98 በመቶ ሲሆን ከፍተኛው የጨለማ መጠን በላልይበላ እንደሚከሰት ገልጸዋል።

ክስተቱን ለማየት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያሻው ገልጸው፤ እስካሁን ለአንድ ድርጅት የመመልከቻ መነጸር ፈቃድ መሰጠቱንና ኢንስቲትዩቱ በራሱ ውስን መመልከቻ መነጽሮች ማሰራጨቱን ገልጸዋል።

ይሁንና ከሰው የማየት ፍላጎት ጋር አቅርቦቱ ስለማይጣጣም በአካባቢያችን ሊገኙ በሚችሉ ቀላል ነገሮች በማዘጋጀት መመልከት እንደሚቻል አማራጭ አቅርበዋል።

ከነዚህም መካከል ቀላል ካርቶን ጥቁር ቀለም በመቀባት ጨረር እንደማያስገባ በማረጋገጥ፣ ሰፋፊ አረንጓዴ የዛፍ ቅጠሎችን ከሰል በመቀባት፣ የፊልም ቁርጥራጮች በመጠቀምና መስኮትን በመሸፈን መጠቀም የሚሉትን ለአብነት አንስተዋል።

ካሜራን ሳይሸፍኑ ክስተቱን ለመቅረጽ መሞከርም ጉዳት እንዳለው አስጠንቅቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም