የአረንጓዴ ልማት ለጤናማ አኗኗር ወሳኝ ግብዓት ነው

65

ሰበታ፣  ሰኔ 11/2012 (ኢዜአ) የልዩ ዞኑ የአረንጓዴ ልማት ለመዲናይቱ ጤናማ አኗኗር ወሳኝ ግብዓት ነው ሲሉ የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለፁ ።

በኦሮሚያ ክልል ሴቶች ፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስተባባሪነት የልዩ ዞኑ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዛሬ በችግኝ ተከላና በደም ልገሳ መርሃ ግብር በይፋ ተጀምሯል ።

በሰበታ ሀዋስ ወረዳ ደበል ተራራ በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና የደም ልገሳ ፕሮግራም ላይ የተገኙት ዋና አስተዳዳሪው አቶ ግርማ ኃይሉ እንደገለፁት የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን በኢንዱስትሪና በህዝብ ብዛት ከሌሎች ከተሞች በተለየ መልኩ የተጨናነቀ ነው ብለዋል ።

ይህንኑ ተከትሎ ከሚከሰተው የአየር መበከልና  የአካባቢ መራቆት መዳን የሚችለው ደግሞ በአረንጓዴ ልማት መሆኑን የሚገልጹት አቶ ግርማ ህብረተሰቡ ለአረንጓዴ አሻራው ጥሪ ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል ።

ከአምናው ተሞክሮ በተሻለ ለመንቀሳቀስ ታስቦ 180 ሺህ ወጣቶች የሚሳተፉበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዛሬ በይፋ መጀመሩን የሚናገሩት ደግሞ የልዩ ዞኑ ሴቶች ፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዝናሽ አቤቤ ናቸው።

ለዘንድሮው ክልል አቀፍ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዞናቸው  ከችግኝ ተከላና ደም ልገሳ በተጨማሪም አምስት የስራ ፕሮግራሞች እና አስራ ስድስት የስራ ዓይነቶችን ለማከናወን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል ።

በተለይም የኮረና ወረርሽኙ ስጋት በሆነበት በዚህ ዓመት የወጣቶቻችን የመልካም አምባሳደርነት ተምሳሌት ከመቼውም ጊዜ በላይ ይፈለጋል ብለዋል።

ዞኑ በአረንጓዴ ልማት  መልካም ተሞክሮ አለው የሚሉት የዞኑ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫላ አደሬ  በበኩላቸው በመደበኛውና በአገር አቀፍ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ከ75 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዛሬ በይፋ ጀምረናል በለዋል።

ተራቁቶ ይታይ የነበረው የደበል ተራራ ዛሬ ለምልሞ መታየቱ በዞኑ አምና ከተተከሉት ችግኞች መካከል ከ90 በመቶ በላይ መፅደቃቸውን ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል ።

ከሱሉልታ ወረዳ ጫንጮ ከተማ የመጣውና የፕሮግራሙ ተሳታፊ ወጣት አበበ ደበላ በበኩሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብዙ ጊዜ የተሳተፍኩበትና የህሊና እርካታ የሚሰጠኝ ተግባር በመሆኑ በየዓመቱ ለመሰማራት ፈቃደኛ ነኝ ይላል።

በዞኑ ካሉ ልዩ ልዩ ወረዳዎች የመጡ ወጣቶችና አመራሮችም በችግኝ ተከላው ከመሳተፍ በተጨማሪ የደም ልገሳና ለችግረኛ ቤተሰቦች የአልባሳትና የሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም