በደቡብ ክልል በ2011 በጀት ዓመት 11 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል

52
ሀዋሳ ሀምሌ1/2010 የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን በ2011 በጀት ዓመት 11 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ። ባለስልጣኑ ባለፉት ዓመታት ስኬታማ የሆነበትን የአንድ መስኮት አገልግሎት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተደራጀ አግባብ እንደሚያጠናክርም አስታውቋል፡፡ የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ አስረስ እንዳሉት በገቢ ግብር አዋጅ መሰረት የደረጃ "ሐ" ፣ "ለ" እና "ሀ" ግብር ከፋዮች ከሐምሌ አንድ ቀን ጅምሮ እስከ ጥቅምት 30ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ዓመታዊ ግብር ከፍለው ያጠናቅቃሉ፡፡ ለዚህም ከማዘጋጃ ቤቶችና ከንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት በቂ ዝግጀት መደረጉን ነው የገለጹት፡፡ "በንግድ ዘርፍ 23 ሺህ አዳዲስ ግብር ከፋዮችን ጨምሮ 226 ሺህ ግብር ከፋዮች ሳይንገላቱና ሳይጨናነቁ እንዲከፍሉ ይደረጋል" ብለዋል፡፡ ባለስልጣኑ ባለፉት ዓመታት ስኬታማ ሆኖበታል ያሉትን የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በብዛት በማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ተግባራዊ እንዲሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከሐምሌ እስከ ጥቅምት ባለው ተመሳሳይ ወቅት 390 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ያስታወሱት አቶ ንጉሴ፣ ዘንድሮ በተመሳሳይ ጊዜ 800 መቶ ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡ ዝግጅቱ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ2011 በጀት ዓመት ከመደበኛና መደበኛ ካልሆነ ግብር ለመሰብሰብ ያቀደውን 11 ቢሊዮን ብር ለማሳካት የሚያስችል መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡ "ያለፈው ዓመት አፈጻጸም በክልልም በአገር አቀፍ ደረጃም ሲገመገም ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከ2010 ግብር እስካሁን 8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አመልክተዋል፡፡ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ ላይ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ያመለከቱት አቶ ንጉሴ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ግብር ከፋዮች በሚመለከተው አካል ተጠርቶ በሚመጣው መረጃ መሰረት ከግብር ነፃ የሚሆኑበትና በአስተያየት ቅናሽ የሚደረግበት አሰራር እንደሚከተሉም ተናግረዋል፡፡ አንድ አካባቢ በተፈጠረ ችግር ሁሉም ግብር ከፋይ የችግሩ ተጠቂ ነው ብሎ እንደማይገመትና ይህንን የሚያደርጉ ግብር ከፋዮች ካሉ ተገቢ አለመሆኑን በክልል ደረጃ ውይይት መደረጉን አቶ ንጉሴ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም