በሲሚንቶ አቅርቦትና ዋጋ ጭማሪ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ መፍትሄ እስኪገኝ ይቀጥላል

49

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11/2012 ( ኢዜአ) መንግስት በሲሚንቶ አቅርቦት ማነስና የዋጋ ጭማሪ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ዋጋውና አቅርቦቱ ወደ ነበረበት እስከሚመለስ እንደሚቀጥል የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የንግድ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በሙገር፣ ደርባ እና ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ ከፋብሪካው ኃላፊዎች ጋርም መክረዋል።

በመስክ ምልከታውም ይሁን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባደረገው ክትትል ለሲሚንቶ አቅርቦትና ዋጋ መጨመር ምክንያት ሆነው የተገኙት፤ በፋብሪካዎቹ  የምርት መስተጓጎል በመከሰቱና ህገ-ወጥ ነጋዴዎች በምርት ሥርጭቱ ላይ በመግባታቸው ነው ብለዋል።

ፋብሪካዎቹ በአሁኑ ወቅት ጥገናቸውን ጨርሰው ወደ ማምረት የገቡ ሲሆን፤ የዋጋ ተመናቸውን ለማስተካከል አሠራራቸውን እንዲመረምሩም ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ ይቻል ዘንድ የማምረቻ ወጪን የሚያሳይ መረጃ እንዲያዘጋጁም ከፋብሪካዎቹ ኃላፊዎች ጋር ስምምነት ተደርሷል።

የመለዋወጫ እጥረት፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥና የኃይል መዋዥቅ ከፋብሪካዎቹ ኃላፊዎች የተነሱ ችግሮች ነበሩ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በመንግሥት በኩል ድጋፎች እንደሚደረጉና ከላይ የተጠቀሱት ችግሮችም እንደሚፈቱ ቃል ገብተውላቸዋል።

ፋብሪካዎቹ በአሁኑ ወቅት ከ70 እስከ 100 በመቶ የአገር ውስጥ ድንጋይ ከሰልን መጠቀማቸውን በመስክ ምልከታ እንዳረጋገጡ ጠቅሰው ይህም ለዋጋ መረጋጋቱ የራሱ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

ሲሚንቶ የግንባታ ዘርፉ ችግር ብቻ ሳይሆን "በስሩ ብዙ ሰራተኞችን የያዘ በልቶ የማደርና ያለ ማደር ጉዳይ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ በተጀመረው ክትትል፣ ድጋፍና ህግ የማስከበር ስራ ዋጋውን በቅርብ ጊዜ እናስተካክላለን ብለዋል።

በመሆኑም ፋብሪካዎቹ የሚገጥሟቸውን ችግሮች የመደገፍና በስርጭቱ ውስጥ የሚገቡ ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን ማስቆም የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ ተግባር ላይ ውሏል ነው ያሉት።

በተለይ ምርቱ ሳይመረት ቀድመው የሚከፍሉ ደንበኞች ህጋዊ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ፣ለምን ተግባር እንደሚያውሉት መከታተልና ህገ-ወጥ የሆኑትን ወደ ህግ የማቅረብ ስራው ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎችም የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በፋብሪካዎቹ ቅጥር ግቢ ችግኝ ተክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም