ሰልጣኞች ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳት በተሰማሩበት ሙያ በግላቸው ስራ ለመፍጠር የመንግስትን ድጋፍ ይሻሉ

121
አዲስ አበባ ሐምሌ 1/2010 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳት በተሰማሩበት መስክ ስራ ለመፍጠር የመንግስትን ድጋፍና ክትትል እንደሚፈልጉ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተመራቂ ሰልጣኞች ገለጹ። በኢትዮጵያ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳት ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን የሰው ሃይል ለማፍራት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ሰልጣኞች ይመረቃሉ። አፈጻፀሙ ከ70 በመቶ ባይበልጥም መንግስት በየዓመቱ 80 በመቶ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሰልጣኞችን በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የማስቀጠር ዕቅድ አለው። በአንፃሩ መንግስት የ10ኛ ክፍል ፈተና ከሚወስዱ ተማሪዎች 20 በመቶው ወደ 11ኛ ክፍል ቀሪዎቹ ወደ ቴክኒክና ሙያ እንዲገቡ ፖሊሲ ቢያስቀምጥም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቅበላ አቅም በማደጉ ወደ 11ኛ ክፍል የሚገቡት ተማሪዎች ቁጥር 35 በመቶ ደርሷል። የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኖች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከተመረቁ በኋላ ስራ ከመፈለግ ይልቅ በተመረቁበት ሙያ የግል ስራ መስራት የተሻለ አማራጭ ነው። በቂርቆስ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የአይ.ሲ.ቲ ደረጃ አራት ተመራቂዋ ቅድስት ደጀኔ በሰለጠንኩበት የሙያ ዘርፍ የግል ስራ በመፍጠር ከኔም አልፎ አገሬን ለማገልገል የመንግስትን ድጋፍ እሻለሁ ብላለች። "በግል መስራት የተሻለ መሆኑን አውቃለሁ፤ ውጤታማ ለመሆን ግን የመንግስት ድጋፍና ክትትል አስፈላጊ ነው" ብላለች። በዚሁ ኮሌጅ በደረጃ አራት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ተመራቂ የሆነችው ማስረሻ ታደሰ ከተመራቂ ጓደኞቿ ጋር በመሆን በግል ለመስራት ከወዲሁ የቢዝነስ እቅድ ማወጣታቸውን ትናገራለች። ይሁን እንጂ ወጣቶቹ ያላቸው እውቀት ተጠቅመው በግል ለመስራትና ውጤት ለማምጣት በቂ ገንዘብ ስለሌላቸው መንግስት የብድር አቅርቦት ሊያመቻችላቸው እንደሚገባ ገልጻለች። ማስረሻ ታደሰ በደረጃ አራት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ሰልጣኝ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግላቸውና ማበረታቻ እንዲሰጣቸው የሚፈልጉ ተማሪዎች መኖራቸውን ገልጻ በቅንጅት ቢሰሩ ውጤታማ የመሆን ተስፋ እንዳላት ተናገራች፡፡ ጴጥሮስ ሰለሞን በደረጃ ሶስት የጋርመንት ሰልጣኝ በበኩሉ በጋራ በመሆን ቢገሰሩ ልምድ እየቀሰሙ በገቢም በእውቀትም እድገት ማምጣት እንደምችሉ ተናግሯል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሰልጣኞች በግላቸው እንዲሰሩ መንግስት ወጣቶችን በማበረታታት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ካደረገ ሰልጣኞች ለለውጥ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የደረጃ አራት የሜታል ኢንጂነሪንግ ሰልጣኝ አንድሰው አየለ በአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚፈልግ ተናግሯል። የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሰልጣኞች ተቀጥሮ የመስራት ፍላጎት ቢኖራቸው እንኳ የኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት በማጥናት በግል ለመስራት መዘጋጀት እንዳለባቸው ገልጿል። መንግስት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሰልጣኞችን በፈጠራ ስራቸው በማበረታታት ተደራጅተው እንዲሰሩ የሚያመቻች ከሆነ እድሉን ለመጠቀም ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም