የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የአስመራ ጉብኝት በዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዕይታ

2706

ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በተባረ ክንዳቸው አምባገነኑን የደርግ ስርዓት መገርሰሳቸውን ተከትሎ ኤርትራ ግንቦት 16 ቀን 1985 ዓ.ም በህዝበ ውሳኔ ራሷን የቻለች ሀገር ሆናለች፡፡

ይህ በሆነ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ግን በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ከሁለቱም ወገን በኩል ደም ያፋሰሰ፣ አካል ያጎደለና ንብረትም ያወደመ ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡

ሰኔ 11 ቀን 1992 ዓ.ም ሁለቱ ሀገራት ጦርነቱ በሁለቱም ሀገራት በኩል እያስከተለ ያለውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ለመግታት የተኩስ አቁም ስምምነት አደረጉ፤ ታህሳስ 3/1993 ዓ.ም ደግሞ ሀገራቱ የአልጀርሱን የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ይሁን እንጂ የአልጀርሱ የሰላም ስምምነት በተለያየ ምክንያት ተግባራዊ ባለመደረጉ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንደሻከረ ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ ሆናቸው፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ ጊዜ ለህዝብ ተወካዮች ባድረጉት ንግግር የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ትኩረት እንደሚሰጠው  ተናግረው ነበር፡፡

ብዙም ሳይቆይ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማደስና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያመች ዘንድም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአልጀርሱ የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ይህን ተከትሎ ደግሞ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው የተመራ ከፍተኛ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል፡፡

ለዚህ ልዑክ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ታዋቂ ሰዎች፣ አርቲስቶች፣ አትሌቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ለዓመታት የተሰቀለው ጥቁር መጋረጃ ለመቀደዱ ምክንያት የሆነው የኤርትራ ልዑክ የገራቱን ግንኙነትና ትብብር ማደስ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከመመካከሩም ባሻገር የሀገሪቱን የልማት ስራዎች ተዘዋውሮ ጎብኝቶ ተመልሷል፡፡

በዛሬው ዕለት ደግሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን፣ የሁለቱን ምክር ቤቶች አፈጉባዔዎች፣ የአፋር ክልልን ፕሬዝዳንትና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎቻቸውን አስከትለው ከአዲስ አበባ በቀጥታ አስመራ አውሮፕላን ጣቢያ በማረፍ  ሌላኛውን ጥቁር መጋረጃ ቀደዋል፡፡

በቦታው ሲደርሱም የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎችና በርካታ ቁጥር ያለው የከተማዋ ህዝብ ደማቅ አቀባበል በማድረግ ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን ፍቅር፣ ክብርና ናፍቆት አሳይተዋል፡፡

ይህን ክስተት በርካታ ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተቀባብለው ዘግበውታል፡፡

ቢቢሲ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የሚያደርጉት ታሪካዊና የመጀመሪያ ውይይት  በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን አለመግባባትና አለመተማመን የማስወገድ አላማ እንዳለው ጽፏል፡፡

ህዝቡና ፕሬዝዳንቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሚመራው ልዑክ ያደረጉትን አቀባበልም በዘገባው አካቷል፡፡

ዋሽንግተን ፖስትም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ጋር ያልተጠበቀ ውይይት ለማድረግ ዛሬ አስመራ መግባታቸውን አስመልክቶ የሀገሪቱን ቴሌቪዥን ጠቅሶ ሰፋ ያለ መረጃ ይዞ ወጥቷል፡፡

ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በጠላትነት ሲፈራረጁ የነበሩ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማደስ ቁርጠኝነታቸውን ባረጋገጡ በቀናት ልዩነት ተጨባጭ ለውጦች መታየት ጀምረዋል፡፡

ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስመራ ሲገቡ ከፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ ጋር የተቃቀፉበትን መንገድና የተለዋወጡትንም ፈገግታ በዘገባው አካቷል፡፡

ሁለቱ መሪዎች የባህል አልባሳትን በለበሱ ሴቶችና የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች የተደረገላቸውን አቀባበልና በአየር መንገዱ ውስጥ በሚገኝ መዝናኛ ክፍል ውስጥ ሁለቱ መሪዎች ጎን ለጎን ተቀምጠው ለስላሳ መጎንጨታቸውንም የዘገባው አካል አድርጎታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአውሮፕላን ጣቢያው ከመውጣታቸው በፊትም ሊቀበላቸው ወደ ተሰበሰበው ህዝብ ቀርበው አክባሪዎቻቸውን አቅፈው ስመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሸከርካሪ ሆነው መሃል አስመራን ሲያቋርጡም ህዝቡ በመንገዱ ግራና ቀኝ ተሰልፎ በጩኸትና በእልልታ እንደተቀበላቸው ዘገባው አትቷል፡፡

ዋሽንግተን ፖስት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን የኤርትራ ጉብኝት አስመልክተው ዛሬ ያሰራጩትን መረጃ ዋቢ አድርጎ እንዳስነበበው ጉብኝቱ በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚቻልባቸውን ጥረቶች ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡

 

ሮይተርስ የዛሬውን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ድንገተኛ የአስመራ ጉብኝት አስመልክቶ እንዳስነበበው የኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች የአስመራ ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል ላለፉት 20 ዓመታት ሰፍኖ ለቆየው የተቀናቃኝነትና ጠላትነት ፍረጃ መቋጫ ያበጅለታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይንና የልዑክ ቡድኑን አባላት የያዘው አውሮፕላን አስመራ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርስ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ያደረጉላቸውን ደማቅ አቀባበልም በዘገባው አስፍሯል፡፡

የዛሬው ስብሰባ በሁለት አስርት ዐመታት ውስጥ በአፍሪካ ቀንድ ሁለት ጎረቤትና ተቀናቃኝ ሀገራት መሪዎች መካከል የተካሔደ የመጀመሪያው ታሪካዊ ስብሰባ መሆኑም በዘገባው ተመልክቷል፡፡

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በተመለከተ የተወሰደው ያልተጠበቀ ውሳኔና እርምጃም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዓለም ዓቀፍ አድናቆትን እንዳተረፈላቸው ያብራራው ዘገባው የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር ያመች ዘንድም ተጨማሪ ማሻሻያዎችን  ለማድረግ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረትም  በዘገባው አካትቷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስመራ መግባት አስመልክተው የኤርትራው ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል “ታሪካዊ ጉብኝት ነው፡፡ ሁለቱ መሪዎች የሚያደርጉት ውይይትም አዲስ የግንኙነትና ትብብር ምዕራፍ ይከፍታል” በሚል በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩትን መረጃ የዘገባው አካል አድርጎታል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን የአስመራ መንገዶችን አጥለቅልቀው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉላቸውን አቀባበልና በመዲናዋ መንገዶች የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከኤርትራ ሰንደቅ ዓለማ ጋር መውለብለቡንም “ተደርጎ የማያውቅ ክስተት” ሲል ዘግቦታል፡፡

በኤርትራ የአሜሪካ ተልዕኮ ኃላፊ በፈገግታ የተሞሉ ኤርትራውያን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያጀቡ ተሸከርካሪዎች በአጠገባቸው ሲያልፉ እጃቸውን ከፍ አድርገው ሲያውለበልቡ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን በትዊተር ገጻቸው ማሰራጨታቸውንም ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡