በአማራ ክልል ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዝ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ሥራ ጀመረ

51

ባሕርዳር፣ ሰኔ10/2012 (ኢዜአ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል አቋቁሞ ዛሬ ሥራውን  ጀመረ።

ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በባሕርዳር ከተማ የተቋቋመው የማስተባበሪያ ማዕከሉ ሥራ መጀመሩን ይፋ በተደረገበት ሥነሥርዓት ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ እንዳሉት የቫይረሱ ሥርጭት በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ እየጨመረ መጥቷል።

በሽታው ከተከሰተ ጀምሮ ግብረ ኃይልና ዘጠኝ መሥሪያ ቤቶችን ያቀፈ ኮሜቴ በማቋቋም መሥራት በመቻሉ ቫይረሱ ተስፋፍቶ ቀውስ እንዳይፈጥር የሚያስችል ውጤት ቢገኝም አሁንም እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በሣምንት አንድና ሁለት ጊዜ በመገናኘት ከመምራት ይልቅ 24 ሰዓት ሙሉ አገልግሎት የሚሰጥ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ማቋቋሙ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ብለዋል።

የማዕከሉ ዓላማም በየደረጃው ያለውን ዕውቀት፣ ጉልበት፣ ሀብትና ፀጋ በማስተባበርና በመምራት ኮሮና በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫና ለመከላከል መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም የፌዴራል ባለድርሻ አካላትና የዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ትብብርን በመጠቀም እስከ ታች ድረስ ያሉ መሠረታዊና በየዕለቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ይኖርበታል ብለዋል።

የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ስትራቴጂክ በሆኑና ውሳኔ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮር የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው በዕለት ተዕለት ሥራዎች ላይ ከማዕከሉ ጋር በሣምንት ሁለት ጊዜ እየተገናኘ እንደሚገመግም ዶክተር ፈንታ ገልጸዋል።

የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አማካሪ አቶ ሙሉነህ ወልደማርያም በበኩላቸው የክልሉ አመራር ኮሮናን በመከላከል እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት ማዕከሉ ውጤታማ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ማዕከሉ የተደራጀው ባለድርሻ የሆኑ ተቋማትን በማካተት በመሆኑ በለይቶ ማቆያ አካባቢዎችና ቀበሌዎች ደረጃ የሚገጥሙ የኮሮና መከላከል ችግሮችን በቀላሉ መፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ለዚህም ክልሉ እስከ ቀበሌ ድረስ የተጠናከረ የቅድመ አደጋ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የተገኘው የእስከሁኑ መልካም ተሞክሮ ለማዕከሉ ውጤታማነት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው።

የማዕከሉ አስተባባሪ አቶ ዘላለም ልጃለም በበኩላቸው የተቋቋመው ማዕከል ከሚመለከታቸው 16 ተቋማት የተውጣጣና ለሥራው ብቁ ናቸው ተብለው የታመነባቸው ባለሙያዎች ተመድበውለት ሥራ መጀመሩን አረጋግጠዋል።

ማዕከሉም የትግበራ፣ የዕቅድ፣ የሎጅስቲክና የፋይናንስ የሥራ ክፍሎችን በማደራጀት ወደ ሥራ መግባቱ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት የሚያከናውናቸው  የኮሮና መከላከል ተግባራት ለማሳካት የሚያስችለው ነው ብለዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ በተለይም በምዕራብ ጎንደርና ምሥራቅ አማራ አካባቢዎች ከሱዳንና ከሌሎች ክልሎች የሚመጡ ወገኖችን ወደ ለይቶ ማቆያ በማስገባት የምግብ፣ መጠለያና ሌሎች ፍላጎቶች ለማሟላት የመረጃ ቅብብሎሹ ፈጣን ያደርገዋል።

በኢትዮጵያ  እስካሁን አጠቃላይ 197 ሺህ 361 የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ  ቫይረሱ  የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 3, 759  መድረሱን የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም