በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በቅንጅት መስራት ይገባል

82

ፍቼ፣ ሰኔ 10/2012 (ኢዜአ ) የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ በሴቶችና ህጻናት ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አሳሰበ።

ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ድርጅት ጋር በመተባበር ባገኘው 200ሺህ ብር ወጪ ያመቻቸው የምግብ ድጋፍ በፍቼ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 200 ሴቶች ዛሬ አበርክቷል።

የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ  በዚህ ወቅት  እንዳሉት  የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ በቤት ውስጥ የሚውሉ ሴቶችና ህጻናት ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ አስገድዶ መደፈር እና  የኃይል ጥቃቶችን ለመከላከል ቤተሰብ፣ የፍትህ አካላትና ሌሎችም አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል።

የቫይረሱን ስርጭት ከመከላከል ውጭ ጥቃት ይፈጸማል ተብሎ አለመገመትና ቸልተኛነት ደግሞ ችግሩ እንዲባባስ ሊያደርጉ የሚችሉ ምከንያቶች በመሆናቸው ሊወገዱ ይገባዋል ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ሴቶችና ህጻናቱ ለመሰል ጥቃቶች እንዳይጋለጡ  ተጎጂዎችም ካሉ  ህክምናና ፍትህ  ቶሎ እንዲያገኙ ከማድረግ አንስቶ በመፍትሔው ዙሪያ  ሁሉም አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የግራር ጃርሶና ፍቼ አካባቢ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወይዘሮ ፀሐይ ደምሴ  በበኩላቸው ከቤተሰብ አንስቶ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍል ኮሮናን ከመከላከል ጎን መሰል ጥቃቶችን መከላከል እንዳለበት አሳስበዋል።

በፍቼ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ሴቶች የተበረከተው ድጋፍ ለአንድ ወር ቀለብ የሚሆን የምግብ ዘይት፣ ሩዝና ዱቄት መሆኑ ተመልክቷል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል በፍቼ የቀበሌ አራት  ነዋሪ ወይዘሮ ፍሬህይወት ሂርጳ በሰጡት አስተያየት የነበራቸው ስራ  በበሽታው ምክንያት በመቆሙ ለችግር ተጋልጠው መቆየታቸውን ካወሱ በኋላ ለተደረገላቸው ድጋፍ  ምስጋና አቅርበዋል።

የ63 ዓመት እድሜ ያላቸው ወይዘሮ አስናቀች ደምሴ  በበኩላቸው  የተሰጣቸው ድጋፍ ችግራቸውን ለማቃለል እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም