በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በበጎ ፈቃደኞች የዜግነት አገልግሎት መረሃ ግብር ተጀመረ

73

ሐረር፣ ሰኔ 10 / 2012 (ኢዜአ) በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በዘንድሮ ክረምት ከ428ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች የሚሳተፉበት የዜግነት አገልግሎት መርሃ ግብር ዛሬ ተጀመረ።

መረሃ ግብሩ የተጀመረው በዞኑ ኮምቦልቻ ወረዳ ኤጉ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ በችግኝ ተከላ፣ በትምህርት ቤት ማስፋፋያና ጥገና ሥራዎች ነው።

በዚህ ወቅት የዞኑ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አሊካ ነስረዲን እንደገለጹት መረሃ ግብሩ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮችም ይቀጥላል።

ለሦስት ወራት በሚቆየው መረሃ ግብር ከከፍተኛ እስከ ሁለተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከወጣት አደረጃጀቶችና ከሴቶች የተውጣጡ ከ428ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች በ38 ዓይነት የልማት ሥራዎች ይሳተፋሉ ብለዋል።

በዞኑ በሚገኙ ተፋሰሶች ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የዛፍ ችግኝ ተከላ፣ የአረጋዊያን ቤት ማደስ፣ የኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና ሥነ ተዋልዶ ትምህርት ከመረሃ ግብሩ ውስጥ የተጠቀሱ ናቸው።

በተለይ የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል አንጻር ኅብረተሰቡን ማስተማርና ደም ልገሳ እንደሚገኙበት ያመለከቱት ወይዘሮ አሊካ በቆይታቸውም ከ50 ሚሊዮን ብር የሚገመት አስተዋጽኦ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የበጎ ፍቃድ ሥራውን ያስጀመሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሶ በበኩላቸው በተለይ ወጣቶችና ሴቶች የአካባቢያቸውን ሰላም የማረጋገጥ፣ የኮሮና ቫይረስን የመከላከልና ቫይረሱ ባስከተለው ተጽዕኖ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የመደገፍ ሥራን በትኩረት እንዲያከናውኑም ጠይቀዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ኅብረተሰቡ ለግንባታው የድርሻውን እንዲወጣ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አቶ ሁሴን አስታውቀዋል።

በኮምቦልቻ ወረዳ መልካ ራፉ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ወጣት አሚ አብዱልሰመድ በሰጠው አስተያየት  ከአሁን ቀደም በተሳተፈባቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሥራ ፍቅር እንዲያዳብርና ሌሎችን የመርዳት ልምድ እንዲያጎለብት ያገዘው መሆኑን ተናግሯል።

ዘንድሮም ኮሮናን  የመከላከልና አቅመ ደካሞችን የሚደግፉ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጿል።

አንድነትንና ፍቅርን በማጠናከር ከዚህ ቀደሙ ከነበረው በተሻለ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከልና ደም ልገሳ ላይ ለመሳተፍ መዘጋጀቷን የተናገረችው ደግሞ ወጣት ሀጃ ኡስማን ናት።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ሥነሥርዓት  የዞንና የወረዳ አመራሮች፣  የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም