ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኤርትራ መግባታቸው ለአገራቱ ሰላም አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው-ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን

99
አዲስ አበባ ሀምሌ1/2010 የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ የሚያደርጉት ጉብኝት በአገራቱ መካከል ሰላም ለማምጣት ሚናው የጎላ መሆኑን ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘገቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ለሃያ ዓመታት የነበራትን "ሞት አልባ ጦርነት" ወደ ሰላም ለመቀየር እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይታወሳል። ይህንንም እውን ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ አስመራ መግባታቸውን የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ለሁለቱ አገራት ሰላም በማምጣት ረገድ በአዎንታዊ መልኩ ተመልክተውታል። ሽፋን ከሰጡት መካከል ቢቢሲ፣ ሮይተርስ፣ አልጀዚራና ዋሺንግተን ፖስት ይገኙበታል። መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባቸው "ከሃያ ዓመት በኋላ ኤርትራን በመጎብኘት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሪ ሆኑ"  ሲሉም ተሰምተዋል። "የሁለቱ ተቀናቃኝ አገራት ታሪካዊ ግንኙነት" በማለት የገለጸው ሮይተርስ የዜና ወኪል ለሃያ ዓመታት በወታደራዊ ተጠንቀቅና በጥንቃቄ ሲተያዩ የነበሩት የሁለቱ አገራት መሪዎች ግንኙነት እጅግ ታሪካዊ መሆኑን አትቷል። ለጉብኝቱ የኤርትራ መንግሥት ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥቶ ከሳምንት በፊት ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት ሲያደረግ ቆይቷል ሲሉም በዘገባቸው ጠቅሰዋል። በርካታ ኤርትራውያንም ወደ አደባባይ ወጥተው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ያላቸውን አክብሮት እንደገለጹና የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰንደቅ አላማዎች ጎን ለጎን መውለብለባቸውን ጠቁመዋል። በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር እስጢፋኖስ አፈወርቂን ጠቅሶ የዘገበው ቢቢሲም "አቀባበሉ በኤርትራ ታሪክ ለማንኛውም መሪ ያልተደረገ" መሆኑን ገልጿል። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ለተቀረው ዓለም ክፍት ለማድረግ ከፍተኛ ለውጥ ማድረጋቸውንም አክለዋል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጉዘው አስመራ ያረፉት ዶክተር አብይ ከአየር ማረፊያው እስከ ቤተ መንግስት በኤርትራውያን ታጅበው  መድረሳቸውንም እንዲሁ። ዋሺንግተን ፖስትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለበርካታ ዓመታት ከአገራቸው ጋር በጠላትነት ከሚተያዩት ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ለመነጋገር ኤርትራ ገብተዋል ብሏል። በተመሳሳይ ኤርትራ ሲደርሱም ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መተቃቀፋቸውንና በርካታ ህዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ እንደተቀበላቸውና በአደባበዮች ላይም የአገራቱ ሰንደቅ ዓላማም ጎን ለጎን መውለብለቡን ነው ያተተው። ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ የኤርትራ ግንኙነት በአዎንታዊ መልኩ መቀየሩም ጉዳዩን በሚከታተሉ በበርካታ ሰዎች ላይ አግራሞት መጫሩንም አንስቷል ዘገባው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሚያደርጉት ውይይት በአገራቱ መካካል የነበረውን የቀድሞውን ሰላም ለማስመለስ ሚናው የጎላ መሆኑን አስታውሷል። አልጀዚራም በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤርትራ ጉብኝት ታሪካዊና አገራቱ ወደ ሰላም ለመመለስ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አስፍሯል። በተለይም በፌስቡክ የተላለፉ አስተያየቶችን ጠቅሶም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የአገራቱን ሰላም በማረጋገጥ በህዝብ ዘንድ እጅግ ትልቅ ግምት የሚሰጠው መሆኑን አስረድቷል። እንዲያውም ከአዲስ አበባ በጉዳዩ ላይ ባለሙያም አነጋግሮ " አገራቱ በጋራ ያላቸው ታሪክ በተናጠል ካላቸው ታሪክ ይልቃል " ብሎ መናገሩን ጠቁመዋል። አገራቱ የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ኃይማኖትና በጋራ ችግሮችንም ማለፋቸውን እንዲሁም አገራቱ በማኅበራዊ፣ በምጣኔ ኃብትና በፖለቲካው ያላቸው አጋርነት ለቀጣንውም የሚጠቅም መሆኑን ዘገባው ባለሙያውን ጠቁሞ አስፍሯል። ጉብኝቱን ከነዚህ መገናኛ ብዙሃን በተጨማሪ የኤርትራ ቴሌቪዥን በቀጥታ ሲያስተላልፈው በኢትዮጵያ በኩልም በተለያዩ ሚዲያዎች ትልቅ ሽፋን ተሰጥቶታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም