ከቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፉት 11 ወራት የተገኘ ገቢ ከእቅድ በታች ነው

128

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10/2012 (ኢዜአ) ባለፉት 11 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከ70 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በኢንስቲትዩቱ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ሰርጄቦ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት 11 ወራት ከአጠቃላይ የቆዳ የወጪ ንግዱ 179 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር።

ከዚህም ውስጥ 70 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት የእቅዱን 40 በመቶ ብቻ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው የቆዳ ጓንት፣ ጫማ፣  አልባሳት፣ ቦርሳ፣ ቀበቶና የመሳሰሉት ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች መሆኑንም ጠቁመዋል።

በ2011 በጀት አመት 9 ወራት ወስጥ 119 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሎ እንደነበር አስታው፤ በዚህ አመት አለም አቀፍ ችግር የሆነው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ለዘርፉ መቀዛቀዝና ገቢውም ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በከፍተኛ መጠን ወደ ውጪ ከምትልካቸው ምርቶች መካከል ቆዳና ሌጦ አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ የቆዳ ምርቶች በዋጋና በጥራት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ በመሆናቸው በዓለም ገበያ ተፈላጊነታቸው በመጨመር ላይ እንደሆነም ገልጸው፤ ጣልያን፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ቻይና እና ጃፓን ለኢትዮጵያ የቆዳ ምርቶች ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸውም ተገልጿል።

የሩቅና መካከለኛው ምስራቅ አገራትና የአፍሪካ አገራትም የኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ ምርቶች መዳረሻ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም