የኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረግ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት የዘርፉን ተወዳዳሪነት ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

1330

አዲስ አበባ ሐምሌ 1/2010 የኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የሰው ሃይል በማፍራት የዘርፉን ተወዳዳሪነት ማሳደግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በ2010 ዓ.ም ያሰለጠናቸውን 8 ሺ 930 ተማሪዎችን ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ አስመርቋል።

ከአጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል 5 ሺ 964 ወንዶች ሲሆኑ 2 ሺ 966 ደግሞ ሴቶች ናቸው።

ሰልጣኞች ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ 5 በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የብቃት ማረጋገጫ ወስደው ተወዳዳሪ መሆናቸው የተረጋገጡ ናቸውም ተብሏል።

በስነ-ስርዓቱ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘርዑ ስሙር  የኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት የዘርፉን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ይገባል።

በዚህም ቢሮው በቴክኒክና ሙያ ዘርፎች እውቀት፣ ክህሎትና አስተሳሰብ የተላበሰ ባለሙያ ለማፍራት ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህም መካከል በገበያው ላይ ተወዳዳሪ የሆኑና ኢንዱስትሪው የሚፈልጋቸውን ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አምስት በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ 8ሺ 930 እጩ ተማሪዎችን ማስመረቁን ገልጸዋል።

ሰልጣኞች በሰለጠኑባቸው የሙያ መስኮች ብቁ መሆናቸው ተረጋግጦ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የወሰዱ መሆናቸውንም ሃላፊው ተናግረዋል።

በከተማዋ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትም የሰለጠነና የበቃ የሰው ሃይል ለማፍራትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች ዘመኑ ከደረሰበት እውቀት፣ ቴክኖሎጂና የአሰራር ሂደት ጋር እራሳቸውን ብቁ በማድረግ በስራ ፈጠራ መሰማራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

በቴክኒክና ሙያ ጉልህ ድርሻ ለነበራቸው የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አሰልጣኞች፣ አመራሮች፣ ዲኖች፣ ኢንዱስትሪዎችና የምዘና ማዕከላት በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ላበረከቱት አስተዋዕኦ ምስጋና አቅርበዋል።

መንግስት ለቴክኒክና ሙያ ዘርፎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ዘርዑ፤ በዚህ ዓመት ከተመረቁት መካከል 80 በመቶ የሚሆኑትን ስራ ለማስያዝ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከመንግስት በተጨማሪም ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች ተቋማት ለተማሪዎች የስራ እድል በመፍጠር የድርሻቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው አቶ ዘርዑ አሳስበዋል።

ተመራቂዎችም በተመረቁበት የሙያ መስክ አገራቸውን በታማኝነትና በቅንነት ማገልግል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ተመራቂዎች በበኩላቸው በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ስራ ፈጣሪ በመሆን እራሳቸውንና አገራቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል።

በስነ-ስርዓቱ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።