በኦሮሚያ ክልል 5 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ተዘጋጁ

65

አዳማ፣ ሰኔ 09/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል 5 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን በክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ገለጹ።

በክልሉ በስድስት ክላስተሮች  ከሚገኙት የግንባታ ፕሮጀክቶቹ  መካከል ዛሬ በሞጆ ከተማ  የተመረቁ ይገኙበታል።

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሲጓተቱ የቆዩና በለውጥ አመራሩ ትጋት  በዘንድሮ በጀት ዓመት የተጠናቀቁ መሆናቸው ተመልክቷል።

አቶ አዲሱ አረጋ በሞጆው ምረቃ ስነስርዓት ወቅት  እንደገለጹት መንግስት የማህበረሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ ቃል በገባው መሰረት 4 ሺህ የሚጠጉ ፕሮጀክቶች  ግንባታ  እንዲጠናቀቁ አድርጓል።

"ፕሮጀክቶቹ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን የሚመልሱ ናቸው" ያሉት አቶ አዲሱ፤ በተለይም የመንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና እና ሌሎች የድህነት ቅነሳ መስኮች ትኩረት ያገኙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም ከ12 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ህብረተሰብ  ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አመላክተዋል።

የሞጆ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ መሰረት አሰፋ በበኩላቸው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 57 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን  በመገንባት ለህብረተሰቡ አገልግሎት ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ የድንጋይ ንጣፍና ጠጠር መንገድ፣ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች፣ የህፃናትና እናቶች ህክምና ማዕከል፣ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተጨማሪ ብሎኮች ተገንብተው ለአገልግሎት ከበቁ ፕሮጀክቶች መካከል ይገኙበታል።

የከተማው አስተዳደር የፕሮጀክቶቹን ወጪ  በራሱ ገቢ መሸፈኑን ያመለከቱት ከንቲባዋ፤ በበጀት ዓመቱ ከእቅድ በላይ ገቢ በመሰብሰቡ የበጀት እጥረት ሳያጋጥመው የልማት ፕሮጀክቶችን ግንባታ ማከናወን መቻሉንም ተናግረዋል።

የከተማው ህብረተሰብም ከኮሮና ቫይረስ እራሱን በመጠበቅ በቀጣይ የልማት ስራዎች የዜግነት አገልግሎት እና የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ላይ በንቃት እንዲሳተፍም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም