ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ዘላቂ ጥቅሟን ለማስከበር የተቀናጀ ዲፕሎማሲ ማራመድ አለባት... ምሁራን

128

ሀዋሳ፤ ሰኔ 8/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ዘላቂ ጥቅሟን ለማስከበር የተቀናጀና ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲ ማራመድ እንዳለባት ምሁራን ተናገሩ።

ኢዜአ በአባይ ተፋሰስና  ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተለያዩ ምሁራንን በሃዋሳ  አወያይቷል።

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የፖሊሲ ልማትና ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክልላዊና አካባቢያዊ ጥናት ማዕከል መምህር ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ  በአባይ ተፋሰስ ድርድር በያዘችው አቋም ገፍታ ከቀጠለች ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ትችላለች።

በተለይ አለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም መርህ እንዲከበር ዲፕሎማሲያዊ ጫና ማሳደር እንዳለባትም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ግብፅ ወታደራዊ ጫና፣ የተለያዩ ስጋቶችና ውጥረት በቀጠናው በማሳደር ኢትዮጵያ እሷ ወደ ምትፈልገው መስመር እንድትገባ ግፊት እያደረገችባት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህንን ለመቀልበስ የተቀናጀና ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲ ማራመድ ወሳኝ መሆኑን ነው ዶክተር የሺጥላ የተናገሩት።

ለዚህ ሁለት ቁልፍ መንገዶች እንዳሉ የጠቀሱት  ዶክተር የሺጥላ  አንደኛው በውሃ ዲፕሎማሲ ድርደሩ ግጭትን በማስውገድ ስምምነት የሚያመጣ ስልትን መከተል ነው።

ሌላኛው ፐብሊክ ዲፕሎማሲን በመጠቀም ኢትዮጵያ ተፋሰሱን የማልማት ፍላጎትና ዓላማ ማስረጽ እንደሆነ ጠቁመው በዚህ የግብፅን የረዥም ጊዜ የተዛባ ትርክት ማምከን ይቻላል ብለዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ አድርጋ አለም አቀፉን ማህበረሰቡ ለማሳመን እያደረገች ያለውን ጥረት ባዶ ማስቀረት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሞልቶት ዘውዴ በበኩላቸው ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የምታነሳቸው ጉዳዮች የበዛ ራስ ወዳድነትና አግባብነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

በቅርቡ የሚጀመረው የግድቡ የውሃ ሙሌት ሂደትም ቢሆን የግብፅን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፣የመስኖና የሌሎችንም አቅሟን ይቀንሳል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአባይን ፍሰት ልትጠቀምበት ያሰበችው አንዱና ዋነኛው ለኃይል ማመንጫነት እንደመሆኑ  ውሃው ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ምንም ሳይቀንስ ተመልሶ ወደ ተፋሰሱ የሚቀላቀል በመሆኑ ሙሌቱ በግብፅ እንዲደናቀፍ መፍቀድ አይገባም ብለዋል።

ግብፅ ታላቁን የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ የራሷ የውሃ ማከማቻ የማድረግ "ድብቅ አጀንዳ" እንዳላት የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊና የደቡብ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የውጭ ቋንቋዎች ሚዲያ ሞኒተሪንግ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዳያሞ ዳሌ  ናቸው።

ግብፅ  የኔ ድርሻ ብላ ያስቀመጠችው የውሃ መጠን እንዳይነካባት ፊት ለፊት ከመምጣት ይልቅ ኢትዮጵያ አልቀበልም ያለችውን ውል ቴክኒካል አስመስላ በማቅረብ ግድቡን የራሷ የውሃ ማከማቻ እንዲሆን ድብቅ ፍላጎቷን እያራመደች መሆኑንም ነው የገለጹት።

መንግስት የዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ከመጠቀም ባለፈ የሃገሪቱን መብት ለማስከበር የያዘውን ጠንካራ አቋም ማስቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የውሃ አቅርቦትና አስተዳደር ተመራማሪና የስምጥ ሸለቆ ሃይቆች ጥናት አስተባባሪ ተባባሪ ዶክተር  ምህረት ዶናንቶ በበኩላቸው "ግብፅ ለሚቀጥሉት 1 ሺህ 360 ዓመታት ጥቅም ላይ ልታውለው የምትችለውን የውሃ ክምችት በእጇ ይዛ ነው ከኢትዮጵያ ጋር የምትደራደረው "ብለዋል።

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ለምትጠቀመው የውሃ ሀብት እንደምትደራደር እየታወቀ የሚደርስባት ወቀሳ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።

"ከድሮ ጀምሮ የነበረው ድርድር የሀገራችንን ተጠቃሚነት የዘነጋ ነው " ያሉት ዶክተር ምህረት፤ አሁን ላይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚያበረታታና  ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም