በትግራይ በቤት ውስጥ የሚውሉ ዜጎችን ለማነቃቃት በሁሉም ከተሞች የጤና ስፖርት እየተካሄደ ነው

73

መቀለ፣ ሰኔ 07/2012  ( ኢዜአ) በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስ ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ መኖሪያ ቤታቸው የሚውሉ ዜጎች ከውጥረት ነጻ ለማድረግና ለማነቃቃት በሁሉም የክልሉ ከተሞች የጤና ስፖርት መካሄድ መጀመሩን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የህዝባዊ መሰረት የስፖርት እድገት ዳይሬክተር ወይዘሮ ካህሱ ዜናዊ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ  ተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎች በቤት ውስጥ መዋል ግድ ሆኖባቸዋል።

ለበርካታ ቀናትና ሰዓታት ቤት ውስጥ መቀመጥ የሚያስከትለውን የአእምሮ ውጥረትና ድብርት ለማነቃቃት ቢሮው በክልሉ ከሚገኝ የአካል ብቃትና ጂም ስፖርት ማህበር ጋር በመሆን የአካል እንቅስቃሴ ስፖርት ማካሄድ መጀመሩን ተናግረዋል።

በመቐለ በአንድ የጋራ መኖሪያ ቤት የተጀመረው የአካል ጥንካሬ የማህበረሰብ ስፖርት አሁን በ23 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፣ በመንግስትና የግል  ተቋማትና በየከተሞቹ በሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋፋቱን አስረድተዋል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በየመኖሪያ ቤታቸው ለሚውሉ አዋቂዎችና ህጸናት ከፍተኛ የአእምሮና የአካል መነቃቃት እየፈጠረ  መሆኑን ወይዘሮ ካሕሱ ገልጸዋል።

በሁሉም አካባቢዎች የሚካሄድ የአካል እንቅስቃሴ  በ40  የስፖርትና ጂም  ባለሞያዎች የታገዘ ነው ብለዋል ።

የትግራይ አካል ብቃትና ጅም ስፖርት ማህበር አስተባባሪ ማስተር ሙዑዝ ደስታ በበኩሉ የዜጎችን ሁለንተናዊ ጤንነት ለመጠበቅ የሚያግዙና አካላዊ ጥንካሬን የሚያዳብሩ የስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ  መሆኑን ገልጿል ።

የአካል ጥንካሬ ስፖርት በእያንዳንዱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ብቻ  ከ200 በላይ ህናትና አዋቂዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ ብሏል ።

በማህበረሰብ ስፖርት እንቅስቃሴ ተሳታፊ በመሆናቸው ከጭንቀትና ከአእምሮ ውጥረት በመላቀቅ ደስተኛ እንዳደረጋቸው የተናገሩት ደግሞ የዓይደር  ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አክሊሉ በርኸ ናቸው።

የዚሁ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ጻድቃን ሀይለስላሴ በበኩላቸው ከሶስት ልጆቻቸውና ባለቤታቸው ጋር በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመጀመራቸው ደስተኛ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም