የኮቪድ-19 ተፅዕኖን እየተከላከልን የአረንጓዴ አሻራ ዕቅድን ከግብ እናደርሳለን - ዶክተር ግርማ አመንቴ

68

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የኮቪድ-19 ተፅዕኖን በመከላከል የአረንጓዴ አሻራ ዕቅድን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳዳሩ ይህንን ያሉት የሮሚያ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ከክልሉ የአርንጓዴ አሻራ ምክር ቤት አባላት ጋር ዛሬ በተወያየበት ወቀት ነው፡፡

በውይይቱም በአገርና በክልል ደረጃ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች ለአረንጓዴ አሻራው ትኩረት መስጠታቸው ለዕቅዱ መሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተመልክቷል።

ዘንድሮ በኦሮሚያ ክልል 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱም ነው የተገለጸው።

በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በውይይቱ ላይ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በአገርና በክልል ደረጃ ለአካባቢ ጥበቃው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት በሚፈለገው ደረጃ አልነበረም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ያሉ አመራሮች ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠታቸው ባለፈው ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን አስታውሰዋል።

በተያዘው ዓመትም በክልሉ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱን አስተባባሪው ጠቁመዋል።

በክልል ደረጃ የሚገኙ የአረንጓዴ አሻራ ምክር ቤት አባላትም ለዕቅዱ መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

እንደ ዶክተር ግርማ ገለጻ በክልሉ የኮቪድ-19 ተፅዕኖን በመከላከል የአረንጓዴ አሻራ ዕቅድን ከግብ ለማድረስ እየተሰራ ነው።

ኅብረተሰቡ በኮቪድ-19 ምክንያት እንቅስቃሴው በተገደበበት በአሁኑ ወቅት በቤቱና በአካባቢው ችግኝ በመትከል ለአረንጓዴ አሻራው መሳካት የበኩልን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በኦሮሚያ ክልል የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በበኩላቸው ኅብረተሰቡ ባለፈው ዓመት ያሳየውን ተነሳሽነት ዘንድሮም መድገም ይኖርበታል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ ከተተከሉ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ችግኞች መካከልም 85 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም ዓመት በክልሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ችግኝ ለመትከል በቂ ሔክታር መሬት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የአረንጓዴ አሻራ ምክር ቤት አባላት ክልሉ አምና ያሳየውን ተነሳሽነት ዘንድሮም መድገም እንደላበት ነው የገለጹት።

በችግኝ ተከላ ወቅት ለአገር በቀል ዛፎች ቅድሚያ መስጠትና የአካባቢን ሥነ-ምህዳር መሠረት በማድረግ መተከል እንደሚገባም አመልክተዋል።

በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ላይ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍም የምክር ቤቱ አባላት ጥሪ አቅርበዋል።

የምክር ቤት አባላቱ ከውይይቱ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኝ ተክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም