በደቡብ ክልል የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መረሃ ግብር ተጀመረ

63

ሆሳዕና፣ ሰኔ 6/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የዘንድሮ ክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መረሃ ግብር በሀድያ ዞን ሌሞ ወረዳ በሌሳ ቀበሌ ዛሬ ተጀመረ፡፡

በዚህ ወቅት የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ከፍታው እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት ክረምት በወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተከናወኑት ስራዎች መካከል ችግኝ ተከላና አካባቢ ጥበቃ፣ ትምህርት፣ ጤናና  ግብርና ይገኙበታል።

በዘንድሮ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ካለፉት ዓመታት ስራዎች ምርጥ ተሞክሮዎችን በመጠቀም የተሻለ ለመስራት ታቅዷል።

ከአንድ ሚሊዮን 200ሺህ በላይ በላይ ወጣቶች በተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ፣ ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤናና በመንገድ ደህንነት መስኮች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

ወጣቶቹ ሁለት መቶ ሀምሳ ሚሊዮን ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የራሳቸውን አሻራ እንደሚያሳርፉም ጠቁመዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ህብረተሰቡን በማስተማር እጅ በማስታጠብና በቫይረሱ ምክንያት የተቸገሩ ወገኖችን  በመደገፍ እገዛ እንደሚደረጉም አመልክተዋል።

የዘንድሮው ክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በጥንቃቄ ራስን በመከላከል የሚሰራ መሆኑን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በግልም ሆነ በማህበር ተደራጅተው ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊዋ በዚህም  በማህበረሰቡ ውስጥ መልካም የህይወት ተሞክሮዎችን የሚያዳብሩበት እንደሚሆኑ አሰረድተዋል፡፡

የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ በበኩላቸው በዞኑ የአረንጓዴ አሻራ አንድ መቶ ሀያ አምስት ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ እቅዱን ለማሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ይጠበቃል።

ቀደም ሲልም ወጣቶች ቫይረሱን ለመከላከል ሲያበረክቱ የቆየውም በጎ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ፤

የሴቶችና ህጻናትን ጥቃት በመከላከልም የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

መረሃ ግብሩ ዛሬ ሲጀመር በችግኝ ተከላ የተሳተፈው በሌሞ ወረዳ በሌሳ ቀበሌ ነዋሪ በጎ ፈቃደኛ ሀብታሙ ካሳ በስራ በመሳተፍ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

ህብረተሰቡ ከወረርሽኙ ራሱን እንዲጠብቅ በማስተማር ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለማገዝ እንደሚጥርም ገልጿል።

በደቡብ ክልል ባለፈው ዓመት የክረምት ወራት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከአንድ ሚሊዮን 900ሺህ በላይ ወጣቶች በመሳተፍ  ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም