በነዳጅ እጥረት ምክንያት መቸገራቸውን በመቀሌ ከተማ አሽከርካሪዎች ገለጹ

71

መቀሌ፣ ሰኔ 06/2012 (ኢዜአ) በነዳጅ እጥረት ምክንያት ተንቀሳቅሰው የዕለተ ተዕለት ሥራቸውን ለማከናወን መቸገራቸውን በመቀሌ ከተማ አስተያየትቸውን ለኢዜአ የሰጡ አሽከርካሪዎች ገለጹ።

የትግራይ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ በበኩሉ የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት የሎጂስቲክስ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።

ከአሽከርካሪዎች መካከል የባለሦስት እግር ባጃጅ ባለንብረት የሆነው ወጣት ገብረአምላክ ተስፋይ እንዳለው በመቀሌ ቤንዚን ከጠፋ አራት ቀናትን አስቆጥሯል።

"በተፈጠረው የነዳጅ ችግር ምክንያትም የዕለት ሥራዬን አቁሜያለሁ፤ የዕለት ጉርሴንና ከባንክ የተበደርኩትን ብድር ለመመለስ ተቸግሬያለሁ'' ብሏል።

የሚመለከታቸው አካላት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡም ጠይቋል።

ነዳጅ በነበረበት ወቅትም ቢሆን አስቀድቶ ለመጠቀም በየማደያው የተሽከርካሪዎች ወረፋ ስለሚጨናነቅ ሙሉ ቀን ያለሥራ እንደሚያሳልፉ የተናገሩት ደግሞ  የቤት አውቶሞቢል ተሽከርካሪ ባለቤት አቶ ጌታቸው ሐጎስ ናቸው።

ሌላ የታክስ አሽከርካሪ  ወጣት ዮናስ መስፍን በበኩሉ መቀሌ ከተማ ውስጥ 18 የሚሆኑ የነዳጅ ማደያዎች ቢኖሩም ነዳጅ ማግኘት እንዳልቻለ  ገልጿል።

በተባበሩት የነዳጅ ማደያ ድርጅት የዓዲ-ሐ ቅርንጫፍ ተወካይ አቶ ዝናቡ ዕድል በተጠቃሚዎች ዘንድ እየቀረበ ያለው ችግር ትክክለኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የችግሩ ዋና ምክንያት በሣምንት ሦስት ቀናት ሰርተው በቀሪዎቹ ቀናት አቅርቦት እጥረት ስላለ ያለሥራ ተቀምጠው እንደሚያሳልፉ አስረድተዋል።

ስለጉዳዩ የተጠየቁት የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ተወልደ በሰጡት ምላሽ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ሥጋት በጅቡቲ መስመር ይመጣ የነበረው ነዳጅ እየቀነሰ በመምጣቱ እጥረት ማጋጣሙን ገልጸዋል።

የነዳጅ ማደያዎች ከያዙት ነዳጅ 30 በመቶ ያህሉ ሲቀራቸው አስቀድመው ለኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት በአፋጣኝ  ማሳወቅ ሲገባቸው በሚፈጥሩት ቸልተኝነት በክልሉ በተደጋጋሚ የነዳጅ እጥረት እንደሚያጋጥም  ጠቅሰዋል።

ከኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ጋር  በመነጋገር  የአቅርቦት ችግሩ እንዲፈታ በክልሉ የሎጂስቲክስ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም