የሙስሊሙ የዘመናት የመብት ጥያቄ የሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን የሌሎች እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ጭምር ነበር

62

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5/2012 (ኢዜአ) ''የሙስሊሙ የዘመናት የመብት ጥያቄ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን የሌሎች እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ጭምር ጥያቄ ነበር'' ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ዑመር እድሪስ አስታወቁ፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ ባገኘው እውቅና በመጠቀም በአንድነትና በመከባበር ለአገር እድገት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በአዋጅ እውቅና ማግኘቱን አስመልክቶ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተቀዳሚ ሙፍቲ እንደጠቆሙት፤ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ባለፉት ሶስት ስርዓቶች ጠይቆ ያላገኘውን መብት  በአሁኑ አስተዳደር በአጭር ጊዜ መጎናፀፉ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ታላቅ ድል ነው፡፡

የሙስሊሙ የእውቅና ጥያቄ ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ የሚቀርብና ምላሽ ያላገኘ ጉዳይ እንደነበር ያወሱት ተቀዳሚ ሙፍቲ፤ 'የሙስሊሙ ጥያቄ ለምን አይመለስም' ሲሉ የሌሎች እምነት ተከታዮች ጥያቄውን አብረው ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሰዋል።

''ጥሩ ላደረገ ምስጋናና ማስታወስ ይገባል'' ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የዶክተር አብይ አስተዳደር በአጭር የስልጣን ቆይታው አንኳር የሆኑ  የሙስሊሙን ጥያቄዎች በመመለስ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

''ሙስሊሙ ካገኘው እውቅና ቀደም ብሎ የሙስሊም ባንኮች እንዲደራጁ ከመፍቀድ ባሻገር በአዲስ አበባ አስተዳደር ለ71 መስጊዶች ካርታ መስጠትና በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን መስጊድ ለመገንባት የተረከብነው ቦታ ተጠቃሽ ናቸው'' ብለዋል፡፡

ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች መካከል አብዛኛዎቹ መመለሳቸውን ጠቅሰው፤ ''ሙስሊሙ በአንድነትና በመከባበር ባገኘው እድል ተጠቅሞ የአገር ልማት አጋር በመሆን ከባድ ሀላፊነት መሸከም እንዳለበት ያሳያል'' ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ ዋና ጸሃፊ ሼህ ቃሲም ሼህ መሀመድ ታጁዲን ባቀረቡት መግለጫ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ባገኘው የተሟላ  ህጋዊ ሰውነት በመጠቀም የተሻለ ሀይማኖታዊና መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህን ታሪካዊ እለት በማሰብ ሙስሊሙ ህብረተሰብ አገሩ የምትፈልግበትን ሁሉ ለመወጣት መዘጋጀት እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡

ከሌሎች የእምነት ተከታይ ወገኖች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን አብሮነት፣ መረዳዳት፣ መተሳሰብ መተዛዘንና መከባበርን በማይናወጥ ጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆም ምክር ቤቱ ጥረት እንደሚያደርግ መግለጫው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም