የኤጀንሲው የቴክኖሎጂ ስራዎች ለነባራዊ ችግሮች በራስ አቅም መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ምሳሌ ናቸው- ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል

118

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ መረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከኮቪድ-19 ወረርሸኝ መከላከል ጋር የተያያዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለነባራዊ ችግሮች በራስ አቅም መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ምሳሌ እንደሚሆኑ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ። 

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የአገራዊ ሠላምና ደህንነት ስጋት በመሆኑ የሁሉንም አካላት የተቀናጀ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሻም ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።

ሚኒስትሯ ኤጀንሲው ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ ያከናወናቸውን የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች በኤጀንሲው ተገኝተው ተመልክተዋል።

ከሠላም ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የአገርና ሕዝብ ሠላምና ደህንነትን ከመጠበቅ መደበኛ ተልዕኮው ጎን ለጎን ወቅታዊ ፈተና በሆነው የኮቪድ-19 ወርርሽኝ ምላሽና ዝግጁነት ላይ እያከናወነ ያለውን እንቅስቃሴም አድንቀዋል።

ወረርሽኙ አገራዊ ሠላምና ደህንነትን የሚያውክ እንደሆነ ገልጸው፤ በዚህ ረገድ ኤጀንሲው በኮቪድ-19 ምላሽና ዝግጁነት ላይ ተልዕኮውን እየተወጣ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ተቋሙ አበልጽጎ ለጤና ሚኒስቴር ካበረከተው 'የኢትዮጵያ የተቀናጀ የኮቪድ-19 የመቆጣጠሪያ ስርዓት' መተግበሪያ ባሻገር በሶስት ወራት ወረርሽኙን መከላከል የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አውጥቷል።

ከእነዚህም መካከል የጽኑ ህሙማን መተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎች፣ ከንክኪ ነጻ የእጅ ማፅጃዎች፣ በሰውና ተሽከርካሪዎች ተህዋሲያን ማምከኛ መሳሪያዎችና አይነተ ብዙ የስነ-ተግባቦት መተግበሪያዎች ይገኙበታል።

እነዚህ ያለምንም ተጨማሪ ወጪ በድርጅቱ ባለሙያዎች የተመረቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ ለነባራዊ ችግሮች በራስ አቅም መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ያበሰሩ እንደሆኑም ነው የተናገሩት።

ባለፉት ሶስት ወራት በተቋሙ የተሰሩ ቴክኖሎጂዎች ወቅታዊ ችግሮችን በራስ አቅም ከመቋቋም ባለፈ አገራዊ አቅምን የሚያጎለብቱና ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጡ እንደሆኑም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

የተቋሙ ባለሙያዎችና አመራሮች አገራዊ ጥሪውን ተከትለው ላከናወኑት ተግባር አመስግነው፤ ወደፊትም ለአገራዊ ችግሮች ምላሽ የሚሆኑ የፈጠራ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለወጣቶች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ በትምህርትና ስልጠና ተቋማት በስፋት ወደ ምርት እንዲቀየሩ ማድረግ ይጠበቃልም ነው ያሉት።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በበኩላችው ኤጀንሲው ከአገር መረጃ መረብ ደህንነት ተልዕኮው በተጨማሪ ባለው ባለሙያና እውቀት በመጠቀም ከኮቪድ ጋር የተያያዙ ስራዎች ላይ መሰማራቱን ገልጸዋል።

እስካሁን ለህጻናትና አዋቂዎች የሚሆኑ የተለየ ዲዛይን ያላቸው ቬንትሌተሮች፣ የድንበር አካባቢ የሰዎች እንቅስቃሴዎችና ራሳቸውን በለይቶ ማቆያ ያስገቡ ሰዎችን መቆጣጠሪያ፣ የሳይበር ውድድርና ስልጠና ለመስጠት የሚያስችሉ መተግበሪያዎችና ሌሎች በርካታ የኢንተርኔት ፕላትፎርሞችን በራሱ ሙያተኞች ማበልጸጉንም ተናግረዋል።

ከነዚህም መካከል ደቦ፣ ንስር፣ ጋሻ፣ ኤርጋና ሲርኩኒ የተሰኙ ከመረጃና ደህንነት ጋር የተያያዙ የስነ ተግባቦት መተግበሪያዎች ኢትዮጵያን ለሳይበር ጥቃት የማያጋልጡ፣ በአገር ውስጥ ብቻ የሚያገለግሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እስካሁን ወደ አስር የሚደርሱ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያዎችን ማምረቱንና በቀጣይ ቁጥራቸውን ወደ 100 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በኤጄንሲው የተፈበረኩ ቴክኖሎጂዎች ወደ ምርት ተቀይረው ለወጣቶች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩና ለገቢ ምንጭነት እንዲያገለግሉ ለማድረግም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

ኤጀንሲው ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ ለሚያመርታቸው ምርቶች ግብዓቶችን ከውጭ ለማምጣት በግዥ ስርዓቱ በኩል ያሉ ተግዳሮቶችን መፍታት እንደሚገባም በጉብኝቱ ወቅት ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም