በኦሮሚያ ክልል የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በቅንጅት ሊሰራ ይገባል--የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት

60
አዳማ ሰኔ 30/2010 በኦሮሚያ ክልል እየተባባሰ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከል በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን አስገነዘቡ። “በኔ ስህተት የአንድም ሰው ሕይወት በትራፊክ አደጋ ሊያልፍ አይገባም” በሚል መሪ ቃል በትራፊክ ደህንነት ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ገልመ አባገዳ ተካሂዷል። በዚህ ወቅት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን እንዳስታወቁት የትራንስፖርት ዘርፉ ሀገሪቱ ለተያያዘችው የህዳሴ ጉዞ ስኬታማነት ከፍተኛ ሚና አለው። ''ነገር ግን ለትራፊክ ደህንነት መስፈን የተቀናጀ ስራ ባለመሰራቱ አደጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል'' ብለዋል። በዚህም ምክንያት በዜጎች ላይ የህይወት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ከማስከተሉም ባሻገር በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በተሰሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥፋት እያደረሰ ነው። ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል በሰው ሃይል ቁጥጥርና ሎጂስቲክ ከማሟላት ባሻገር ሁሉንም አካል ያሳተፈ የቅንጅት ስራ ሊዘረጋ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በተለይ ሰፊውን ህዝብ በማንቀሳቀስ ከቀበሌ ጀምሮ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የጋራ ርብርብ ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም አስታውቀዋል። በአንዳንድ የትራፊክ ፖሊስ አባላትና የመንጃ ፈቃድ አሰልጣኝ ተቋማት የሚታየው ሙስና፣ ስነ ምግባር የጎደለው ብልሹ አሰራር ለትራፊክ አደጋ መባባስ ምክንያት ሆኗል ያሉት ወይዘሮ ጠይባ በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት የቅርብ ክትትል በማድረግ የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል። የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ እሼቱ ደሴ በበኩላቸው  በክልሉ ለትራፊክ አደጋ መባባስ ምክንያት የሆኑትን በጥናት በመለየት ለመፍትሄው በጋራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል። የአንድም ሰው ህይወት በትራፊክ አደጋ እንዳይጠፋም የትራንስፖርት ዘርፍ ተዋናዮች ጤናማ የትራፊክ ደህንነት ለማስፈን የህግ ተገዥ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል። የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች የሥራ ሂደት መሪ ወይዘሮ ነፃነት ዓለሙ በክልሉ በቀጣዮቹ 15 ዓመታት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችል ሰነድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። በተዘጋጀው ሰነድ ላይ  መግባባት በመፍጠር ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመግባት ታልሞ መድረኩ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል። በባለሥልጣኑ የመንገድ ደህንነት ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በኦሮሚያ ክልል 3 ሺህ 760 የትራፊክ አደጋ መድረሱን ገልጸዋል። አደጋውም የአንድ ሺህ 717 ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት አውድሟል። ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ ላይ የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ከክልሉ፣ ሁሉም ዞኖችና ዋና ዋና ከተሞች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም