ኢትዮጵያ ያመጠቀቻት ሳተላይት የምታመጣውን መረጃ ለሚፈልጉ አካላት ለመሸጥ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል

89

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያመጠቀቻት የመሬት መመልከቻ ሳተላይት (ETRSS-1) የምታመጣውን መረጃ ለሚፈልጉ አካላት ለመሸጥ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ለኢዜአ እንዳሉት፤  ከዚህ  ቀደም በቻይናውያን ሲከወን የቆየው የሳተላይት ቁጥጥር ስራ በአሁኑ ወቅት ሙሉ  በሙሉ  በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እየተካሄደ ነው።

ጥሩ የእዉቀት ሽግግር በመደረጉ ስራው በኢትዮጵያዊያን አቅም መካሄድ መጀመሩንም ተናግረው፤ የኢትዮጵያውያኑን ዓቅም ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ሳተላይቷ መረጃ መላክ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ደረጃውን የጠበቀ መረጃ ያለማቋረጥ እየተሰበሰበ ነው።

ኢትዮጵያ ሳተላይቷን በማምጠቅ መረጃ ለማግኘት የምታወጣውን ወጪ ከማስቀረት ባለፈ መረጃ በመሸጥ ገቢ ማግኘት መጀመሯን የገለጹት ዶክተር ሰለሞን፤ ሳተላይቷ የምታመጣውን መረጃ ለሚፈልጉ አካላት ለመሸጥ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

የምስል ግዢ ፍላጎት ላቀረቡ አገሮች ምላሽ መስጠት እንደተጀመረም ዶክተር ሰለሞን  አስረድተዋል።

አሰራሩን ቀላል ለማድረግ ጥረት መደረጉንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪዋን የመሬት መመልከቻ 72 ኪሎ ግራም የምትመዝን ‘ETRSS-1’  የተሰኘችውን ሳተላይት ወደ ህዋ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ማምጠቋ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም