ተጨማሪ 245 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፤ የ 7 ሰዎችም ሕይወት አልፏል

60

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 5709 የላብራቶሪ ምርመራ 245 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውና የ 7 ሰዎች ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ፡፡

በዚህም በሀገሪቱ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 2ሺህ 915 ደርሷል።

ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 241 ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ 4 ሰው የውጭ ሀገር ዜጋ መሆናቸው ታውቋል።

በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል 172 ወንድና 73 ሴት ሲሆኑ የዕድሜ ክልላቸው ከ1 እስክ 85 አመት ነው።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል 190 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 16 ሰዎች ከሱማሌ ክልል፣ 3 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 15 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣17 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 4 ሰዎች ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል እንደሆነም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት በቫይረሱ ምክንያት ተጨማሪ የ7 ኢትዮጵያዊያን ህይወት ያለፈ ሲሆን 6ቱ በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው፣ አንዱ ደግሞ በሕክምና ማዕከል ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል።

በዚህም አጠቃላይ በአገሪቱ በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 47 ደርሷል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።

በሌላ በኩል በትላንትናው ዕለት 17 ሰዎች ( 16 ከአዲስ አበባና 1 ሰው ከደቡብ ክልል ) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 451 መድረሱን ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።

በጽኑ ህሙማን ክፍል ህክምና እየተደረገላቸው የሚገኙ 38 ሰዎች መሆናቸው ተገልጿል።
እስካሁን አጠቃላይ በኢትዮጵያ 170 ሺህ 860 የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም