ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት ተመራቂዎች መጣር ይጠበቅባቸዋል

66
አክሱም ሰኔ 30/2010 ተመራቂ ተማሪዎች በሚሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች ለሀገር እድገትና ብልፅግና በመጣር ከድህነት ለማላቀቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ የአክሱም ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት አስገነዘቡ ። ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የስልጠና መስኮች በ51 የትምህርት አይነቶች በቅድመና ድህረ ምረቃ መርሀግብር ያሰለጠናቸውን 3 ሺህ 500 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል። ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው መካከል 39ኙ የህክምና ዶክተሮች መሆናቸውን ተናግረዋል ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጸሃየ አስመላሽ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ተመራቂዎች በሚሰማሩባቸው የስራ መስኮች ለእድገትና ብልፅግና በመጣር ኢትዮጵያ ድህነትን አሸንፋ እንድትወጣ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ። ዩኒቨርሲቲው የቅበላ አቅሙን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ መምጣቱን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ በአሁን ሰአት ከ25 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን እያሰለጠነ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል ። "ዩኒቨርሲቲው በ2011 የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ዲግሪ በትግርኛ፣ ግእዝና አንትሮፖሎጂ  እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪ የፊዚክስ ትምህርት ስልጠና ለመስጠት መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል ። በአድዋ አራተኛው ካምፓስ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት የትምህርት ዘርፍ  ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት ማድረጉን አመላክተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባልና የእለቱ ክብር እንግዳ በኢፌድሪ የቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በበኩላቸው በሃገራችን የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል በክህሎትና እውቀት የተካነ ትውልድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል ። ‘‘የሀገሪቱን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወሰነው በወጣት ምሁራን ነው” ያሉት አቶ ዮናስ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገራቸውና ህዝባቸውን በታማኝነት ሊያገግሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። በዩኒቨርስቲው የሲቪል ኢንጅነሪንግ ተመራቂ ወጣት ዮሃንስ ሐጎስ "ተመርቀን ስንወጣ ሃገራችንና ህዝባችን በቅንነት ለማገልገል ትልቅ ራእይ በመያዝ ነው" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል ። የመንግስት ስራ ሳትጠብቅ የራሷን ስራ በመፍጠር በሃገሯ እድገት ላይ የራሷን አሻራ ለማስቀመጥ ዝግጁ መሆኗን የገለፀችው ደግሞ በኮምፒተር ሳይንስ የተመረቀችው ወጣት ሳሮን ተክላይ ናት። በህዝቦች መካከል የቆየውን የመከባበበርና አንድነት ባህል በማጠናከር ለሰላምና እድገር አርአያ ሆና ለመስራት መዘጋጀቷን አረጋግጣለች ።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም