አፍሪካ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የብሮድባንድ ኢንተርኔት ያስፈልጋታል

72

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 04/2012 (ኢዜአ) አፍሪካ የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በዝቅተኛ ክፍያ ተደራሽ የሆነ የብሮድባንድ ኢንተርኔት እንደሚያስፈልጋት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ገለጸ።

የአህጉሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሳደግ መስራት እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።

በኮሚሽኑ የቴክኖሎጂ፣ አየር ፀባይ ለውጥና የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር ጂን ፖል አዳም  አፍሪካ እንዳሉት ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ፈጣንና ተደራሽ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ሊስፋፋ ይገባል።

አህጉሪቱ በዓለም አጠቃላይ የምርት ዕድገት ውስጥ 15 በመቶ ድርሻ ቢኖራትም፤ በዲጂታል ኢኮኖሚው ዘርፍ ድርሻ ከአንድ በመቶ የማይበልጠውን ድርሻዋ ማደግ አለበት ብለዋል።

በአፍሪካ 250 ሚሊዮን የሚጠጉ ህፃናት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፡ አብዛኛዎቹ በኢንተርኔት የታገዘ ትምህርት እንዳያገኙ የዲጂታል መሣሪያዎች እጥረት ችግር እንደሆነባቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የጤና ተቋማት ፈጣንና አስተማማኝ የኢንተርኔት አገልግሎት ስለሌላቸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚረዱ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን መረጃ ከዓለም አቀፍ የትስስር መረብ ለመገናኘት  እንደሚቸገሩ አስረድተዋል።

የትምህርትና የንግድ ተቋማት መሠረታዊና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት ዘላቂ የብሮድባንድ ትስስር እንደ ሚያስፈልጋቸው ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

አህጉሪቱ በዲጂታል ትስስር ያላት ድርሻ ዝቅተኛ ቢሆንም፤ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢንተርኔት በመታገዝ የሰጠችውን ምላሽ ''ድንቅ'' ብለውታል።

አህጉሪቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ያለው፤ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብና ጥራቱ የተጠበቀ የኢንተርኔት አገልግሎት ለዜጎቿ ለማዳረስ 100 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት አመልክተዋል።

በአፍሪካ በአባወራ ደረጃ ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት 17 ነጥብ 8 በመቶ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 21 በመቶ ድርሻ አላት።

“መረጃዎች እንደሚያሳዩት አምስት ጂቢ መጠን ያለው ፊልም ለማውረድ በኢትዮጵያ 850 ደቂቃ፣ በኢኳቶሪያል ጊኒ 1 ሺ 342 ደቂቃ ሲወስድ፤ በሲንጋፖር ግን 11 ደቂቃ ብቻ ይፈጃል" በማለት ዳይሬክተሩ ልዩነቶችን አሳይተዋል።

በአህጉሪቱ ባለፈው ዓመት በተሰላ የኢንተርኔት ተደራሽነት ወንዶች 33 ነጥብ 8 በመቶ ሴቶች ደግሞ 22 ነጥብ 6 በመቶ ምጣኔ አላቸው።

መንግሥታት ከግል ባለሃብቱ ጋር በመቀናጀት ዘርፉን ለማዘመን መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አፍሪካ አራተኛውን የማምረቻ ዘርፉን ማሳደግና ዘመናዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባት ገልጸዋል።

በተጨማሪ የኢኮኖሚ ስብጥሩን ማስፋትና በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና በመታገዝ ትስስርን ማሳደግ ይቻላል ብለዋል።

ለዚህም አዳዲስና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ኮሚሽኑ ያሰራጨው ዘገባ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም