የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 123 የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት አፀደቀ

67
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2010 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ123 የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት አፀደቀ። ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 49 እንዲሁም ለፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት 74 እጩ ዳኞችን  እንዲሾሙለት ለምክር ቤቱ አቅርቧል። ከቀረቡት ዳኞች መካከል 24ቱ ሴቶች ናቸው። የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አማኑኤል አብርሃም ለህገ መንግስቱ ታማኝ የሆኑ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ፣በዳኝነት በቂ ልምድ ያላቸውን ለመመልመል ከአንድ አመት በፊት በግልፅ ማስታወቂያ እንደወጣ ተናግረዋል። ምልመላው ካለፉት አመታት በተሻለ ጥንቃቄ የተሰራና በትምህርት ዝግጅታቸውም የተሻለ መሆኑን ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የዳኞቹን ሹመት ውሳኔ ቁጥር 21/2010 አድርጎ ያፀደቀ ሲሆን ዳኞቹ በምክር ቤቱ ቀርበው በታማኝነት ለማገልገል ቃለ መሃላ ፈፅመዋል። በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን የጎደሉ የቦርድ አመራር አባላት ለማሟላት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተላኩለትን ሰዎች ሹመት አፅድቋል። የመንግስት ኮሙኒኬሸን ፅህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የኢቢሲ ቦርድ ሰብሳቢ፣ ዶክተር መራራ ጉዲና፣አቶ ፍስሃ ይታገሱ፣ወይዘሮ ሃሊማ ባድገባ የቦርድ አባል ሆነው ተሹመዋል። አቶ አማኑኤል ሹመቱ በተሃድሶ ወቅት የተቀመጠውን አቅጣጫ የተከተለ፣ብዝሃ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ ለማድረግ፣የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም