ምሩቃን በተማሩት የትምህርት ዘርፍ ህዝባቸውን ማገልገል አለባቸው

94
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2010 በኢትዮጵያ አሁን የተጀመረውን መነቃቃት ለማስቀጠል ምሩቃን በተማሩት የትምህርት ዘርፍ ህዝባቸውን በላቀ መልኩ ማገልገል አለባቸው ተባለ። የአትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1ሺህ216 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል። በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አዳሙ አያና እንደተናገሩት፤ በዩኒቨርሲቲው ሰልጥነው የተመረቁት ተማሪዎች ወደ ስራ ሲሰማሩ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማገዝና ህዝብን ለማገልገል ተግተው መስራት አለባቸው። በኢትዮጵያ አሁን የተጀመረውን መነቃቃት ምሩቃን በተማሩት የትምህርት ዘርፍ ህዝባቸውን በላቀ መልኩ እንዲያገለግሉ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርላቸው እንደሆነ ተናግረዋል። ''ተመራቂዎች በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ህብረተሰቡን በላቀ ደረጃ ማገልግል አለባቸው'' ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው። በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ተመራቂዎች የበኩላቸውን በመወጣት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። መንግስት ሲቪል ሰርቫንቱን ለማብቃት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ አዳሙ ጠቁመዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ በበኩላቸው ''ተመራቂዎች በተማሩት ሙያ አገራቸውን በታማኝነት ማገልገል ይኖርባቸዋል'' ብለዋል። ተመራቂዎች እራሳቸውን የበለጠ እያበቁ መቀጠል እንዳለባቸው ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል። በተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው በተማሩት የትምህርት መስክ ህብረተሰቡን የበለጠ ለማገልግል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። አስተያየታቸውን ከሰጡ ተመራቂዎች መካከል ወይዘሮ ሂሩት ገብረኪዳን እንዳሉት በመንግስት ፖሊሲ መሰረት ህብረተሰቡን በላቀ ደረጃ ለማገልግል ተዘጋጅቷል። ሌላው ተመራቂ ተማሪ ሮቤራ አሰፋ በበኩሉ ባገኘው ትምህርት የላቀ አገልግሎት በመስጠት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚታየውን የአገልግሎት ችግር ለመቅረፍ የበኩሉን እንደሚወጣም ጠቁመዋል። ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተበት እ አ አ ከ1995 ጀምሮ እስከአሁን ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች አስመርቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም