የኮሌጁ የኤሌክትሮኒክስ ትምህርት መስጫ (ኢ ለርኒንግ) መተግበሪያ ይፋ ሆነ

114

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 02/2012 (ኢዜአ) የአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ያዘጋጀው ኤሌክትሮኒክስ ትምህርት መስጫ (ኢ ለርኒንግ) መተግበሪያ ይፋ ተደረገ።

መተግበሪያው የትምህርት አሰጣጡን እንደሚያቀላጥፍ ታምኖበታል።

መተግበሪያው በአዲስ አበባ የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በቤታቸው የተቀመጡትን ከ30 ሺህ በላይ ሰልጣኞች ችግር እንደሚያቃልል የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ዳይሬከተር አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ገልጸዋል።

"ኤል ጂ ኮይካ ሆፕ" በተሰኘ ድርጅት ዛሬ ይፋ የተደረገው መተግበሪያ መረጃን በምስል አስደግፎ  ያቀርባል።

በተጨማሪ ከኮቪድ ወረርሽኝ ማብቃት በኋላ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

መተግበሪያው ሰልጣኞች በቤታቸው ሆነው ትምህርታቸውን ለመከታተል ያስችላቸዋል። በቤታቸው ሆነው ጥያቄዎችን እንደሚያቀርቡበትም አስረድተዋል።

በተጨማሪም  ተማሪዎች ከመምህራን ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያዳብር አቶ ዳኛቸው አስረድተዋል።

በከተማዋ የሚገኙት ሁሉም የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት መምህራን በመተግበሪያው አጠቃቀም ላይ ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

የአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ደመላሽ ተስፋዬ መተግበሪያው ቀለል ያለና በምስል የታገዘ በመሆኑ ሰልጣኞች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ከጫኑት በኋላ የመታወቂያ ቁጥራቸውን በማስገባት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉበት ተደርጎ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በተጨማሪ ፈተና በሚወስዱበት ጊዜ ለእያንዳንዱ ጥያቄ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ ስላለው ተማሪዎች ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል።

ተማሪዎች መተግበሪያውን በመጠቀም ያልገባቸውን ጥያቄ ለመምህራቸው በማቅረብ ምላሽ የሚያገኙበት እንዲሁም ከአካላዊና ከወረቀት ንክኪ የፀዳ መሆኑም ተገልጿል።

ድርጅቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2014 ጀምሮ ለችግረኛ ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል በመስጠት እገዛ እያደረገ መሆኑ ተወስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም