የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 7 ሺህ 187 ተማሪዎችን አስመረቀ

77
ጎንደር ሰኔ 30/2010 በመጪው አመት ለሚጀመረው ሀገር አቀፍ የተመራቂዎች የመውጫ ፈተና ተማሪዎችን ለማብቃት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በመደበኛው፣ በተከታታይና በክረምት የትምህርት መርሃግብሮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 7 ሺህ 187 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ እንደተናገሩት ተመራቂ ተማሪዎች በመውጫ ፈተናው አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የተከታታይ ምዘና ስርአቱ በጥብቅ ቁጥጥር እንዲከናወን በመደረግ ላይ ነው፡፡ የተቋሙ ተመራቂዎች ለፈተናው በቂ የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው ከማድረግ አንስቶ ተማሪዎችን በማብቃት ረገድ ክፍተቶችን በመለየትና በመፍታት ካለፈው አመት ጀምሮ ሞዴል የአጠቃላይ ፈተና መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በህግ ትምህርት ዘርፍ ላለፉት ሰባት አመታት የመውጫ ፈተና ሲሰጥ መቆየቱን የተናገሩት ፕሬዘዳንቱ በዚህ አመት ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች 95 በመቶ የሚሆኑት አጥጋቢ ውጤት ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡ በማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ ዘርፍ ትኩረቱን ያደረገው ዩኒቨርሲቲው በዚህ አመት ብቻ በ187 ሚሊዮን ብር ወጪ 150 የምርምር ፕሮጀክቶችን ማከናወን ችሏል፡፡ በበጀት አመቱ 175 የምርምር ስራዎች በታዋቂ ጆርናሎች ለህትመት መብቃታቸውን የጠቆሙት ፕሬዘዳንቱ 15 የምርምር ፕሮጀክቶች ደግሞ ወደ ማህበረሰብ አገልግሎት መሸጋገር እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አመታት በምርምሩ ዘርፍ ካከናወናቸው ችግር ፈቺ የምርምርና የፈጠራ ፕሮጀክቶች መካከልም 11 ያህሉ በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የባለቤትነት መብት አግኝተዋል፡፡ በትምህርት ዘመን ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች አሰልጥኖ ካስመረቃቸው መካከልም 5ሺ 547ቱ በመጀመሪያ ዲግሪ 1ሺህ 640ዎቹ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ ሲሆኑ ከተመራቂዎቹ መካከልም 2ሺ 520ዎቹ ሴቶች ናቸው፡፡ በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌድሪ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዶክተር አምባቸው መኮንን በትምህርት ተኮትኩቶና ተቀርጾ ያደገ ትውልድ ስራ ፈጣሪ፣ ሩቅ አሳቢና ለሀገራዊ ልማትና ብልጽግና የሚተጋ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ ''የወደፊት ስኬታችሁን የምትወስኑት ራሳችሁ በመሆናችሁ በራሳችሁ አቅምና ሃይል በመተማመን በሀገር ግንባታው ዘርፍ የዜግነት ድርሻችሁን ለመወጣት ዝግጁነታችሁን በተግባር ልታስመሰክሩ ይገባል ሲሉ'' ተናግረዋል፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ ሀገርና ህዝብ በእውትና በክህሎት ብቁ ዜጋ እንዲሆን የተሟላ ድጋፍ አድርገውልኛል ያለው በማስተማር ስነ ዘዴ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ የሆነው ተማሪ አለም አሉላ ነው፡፡ በሲቪል የምህንድስና ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀው አለምነህ ሲሳይ በበኩሉ ''በዩነቨርሲቲ ቆይታዬ በቀሰምኩት እውቀት ስራ ፈጣሪ በመሆን ራሴንና ሀገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ'' ብሏል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርአቱ ማብቂያም የከብር እንግዳው በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ተመራቂዎች ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀውን የወርቅ ሜዳሊያና ሽልማት ሰጥተዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቅድመ ምረቃ 82፣ በሁለተኛ ዲግሪ 110፣ በሶስተኛ ዲግሪ 27 የትምህርት ፕሮግራሞች ሲኖሩት በአሁኑ ወቅትም ከ47ሺ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም