በደቡብ ወሎ ዞን 376 የባዮጋዝ ግንባታ ተካሄደ

138

ደሴ፣ ሰኔ 2/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን 376 የባዮ ጋዝ ግንባታ ተካሂዶ ለአገልግሎት መብቃቱን የዞኑ ውኃ መስኖና ኢነርጂ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የአማራጭ ኢነርጂ ልማት ቡድን መሪ አቶ ይርጋለም ደምስ ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የተለያዩ የኃይል አማራጮችን በመጠቀም የገጠሩን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በዚህ በጀት ዓመትም 407 ባዮ ጋዝ ለመገንባት ታቅዶ በ8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ የ376 ባዮ ጋዝ ግንባታ በማካሄድ ለአርሶ አደሩ ጥቅም እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል።

የባዮ ጋዝ ግንባታውን ለማካሄድም መንግሥት የፋብሪካ ውጤቶችንና የባለሙያዎች አቅርቦት ሲያደርግ አርሶ አደሮች ደግሞ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው አስተዋጽኦ አድርገዋል።

የባዮ ጋዝ ልማት ከጭስ የጸዳ መብራትና የምግብ ማብሰል አገልግሎት በመስጠት የገጠሩን ኅብረተሰብ የአኗኗር ሁኔታ ለመለወጥ የሚያስችል መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዓመት እስከ 270 ኩንታል ኮምፖስት የሚያስገኝ በመሆኑ አርሶ አደሩ ለዘመናዊ ማዳበሪያ የሚያወጣውን ወጪ ከማስቀረት ባሻገር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።

በጪስ ምክንያት የሚደርስ የአየር ብክለትን በማስቀረት፣ የደን ጭፍጨፋን በመታደግ፣ የእናቶችን ጉልበትና ጊዜ የሚቆጥብ በመሆኑ አርሶ አደሩ አሁን ላይ ከፍተኛ ፍላጎት እንዲኖረው አድርጓል ብለዋል።

በወረኢሉ ወረዳ የ07 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዘሪቱ አራጋው በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ለምግብ ማብሰያና የማገዶ እንጨት ፍለጋ ረጅም ርቀት በመጓዝ ጉልበትንና ጊዜያቸውን ያባክኑ እንደነበረ ተናግረዋል።

እንጨት ተጠቅመው እሳት ሲያቀጣጥሉ የሚወጣው ጭስ በዓይናቸው ላይ የጤና እክል እየፈጠረባቸው እንደነበር ጠቁመው የቤታቸውን ውበት ጭምር ያበላሽባቸው እንደነበር ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ባዮ ጋዝ አስገንብተው መብራት፣ ስቶቭና የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ በመጠቀማቸው ችግራቸው መቃለሉን ተናግረዋል።

በዚሁ ወረዳ የ04 ቀበሌ ነዋሪ አቶ መሐመድ ይመር እንደገለጹት ከዚህ በፊት ባለሙያዎች ባዮ ጋዝ እንዲገነቡ ምክር ቢለገሳቸውም ፍቃደኛ ሳይሆኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ዘንድሮ ቤተሰቤ ባሳደረብኝ ተፅዕኖ ምክንያት ባዮ ጋዝ በማስገንባቴ በቤት ውስጥ ከማገኘው ጥቅም ባሻገር የሚወጣውን ተረፈ ምርት ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ከሁለት ሺህ በላይ የባዮ ጋዝ ግንባታ በማካሄድ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር መከናወኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም