ተጨማሪ 190 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፤ የ 5 ሰዎችም ሕይወት አልፏል

78

አዲስ አበባ፣ ሰኔ2/2012(ኢዜአ) ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 4599 የላብራቶሪ ምርመራ 190 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውና የ5 ሰዎች ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ፡፡

በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 2ሺህ 336 ደርሷል፡፡

ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ 135 ወንድና 55 ሴት እንዲሁም የዕድሜ ክልላቸው ከ1 እስክ 89 አመት እንደሆነ ታውቋል።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 153 ሰዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፣ 16 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 3 ሰዎች ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል፣ 10 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 3 ሰዎች ከሀረሪ ክልል፤ 3 ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ እንዲሁም 2 ሰዎች ከትግራይ ክልል እንደሆነ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት 5 ሰዎች ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ከሟቾች መካከልም 2ቱ በአስክሬን ምርመራ የተረጋገጠ፣ 3ቱ ደግሞ በሕክምና ማዕከል በሕክምና ሲከታተሉ የነበሩ መሆናቸው ታውቋሏ።

በዚህም አጠቃላይ በአገራችን በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 32 ደርሷል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።

በሌላ በኩል በትላንትናው ዕለት 18 ሰዎች ( 11ዱ ከአዲስ አበባ፣ 5ቱ ከአማራ ክልል፣ 2ቱ ሱማሌ ክል) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 379 መድረሱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት 32 ሰዎች በጽኑ ሕክምና ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል።

የበሽታው ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ክልሎች፣ የከተማ አስዳደሮች እና የሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ሌሎች አካላት የበሽታው ሥርጭት ተስፋፍቶ ከአቅም በላይ ከመድረሱ እና ለከፋ ችግር ከመዳረጋችን በፊት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ከምንጊዜውም በላይ ኅብረተሰቡን ባማከለ እና ባሳተፈ መልኩ አስፈላጊውን የመከላከል ሥራ እንዲተገብሩ በአፅንኦት አሳስበዋል።

እስካሁን በአገራችን አጠቃላይ 152 ሺህ 334 የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም