የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ሽልማት እንዲመለስ አድርጎ እንደማያውቅ ገለጸ

118

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2/2012(ኢዜአ) የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ሽልማት ከሰጠ በኋላ እንዲመለስ አድርጎ እንደማያውቅ አስታወቀ።

ኮሚቴው ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሰጠው ሽልማትም እንደሚገባቸው በማመን መሆኑን ዳግም አረጋግጧል።

ኮሚቴው ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የኖቤል ሽልማት ለአሸናፊዎች ከተበረከተ በኋላ ፈፅሞ እንዲመለስ አያደርግም።

የኖቤል ሽልማት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1901 ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን አንድም ሽልማት እንዲመለስ ያላደረገ መሆኑንም አረጋግጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምስራቅ አፍሪካ በተለይም ለ20 ዓመታት በግጭት ውስጥ የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም እንዲፈጥሩ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ማግስት ጀምሮ በአገራቸው የፖለቲካ እስረኞች ይደርስባቸው የነበረው ኢሰብአዊ ድርጊት እንዲያበቃና እንዲፈቱም አድርገዋል።

በፖለቲካ አመለካከታቸው ከአገራቸው ተሰደው የነበሩ ፖለቲከኞችም ለሰላማዊ ትግል አገር ቤት እንዲገቡ በማድረግ የተሳካ ተግባር መፈፀማቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእነዚህ ስኬቶቻቸው የ2016 የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ ለመሆን መብቃታቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ሰሞኑት አንዳንድ ግለሰቦች "ሽልማታቸው ሊነጠቅ ነው" በሚል የተሳሳቱ ሃሳቦችን ሲያራምዱ ተደምጠዋል።

ኮሚቴው በዛሬው እለት ይፋ እንዳደረገው ከሆነ አሁንም ሆነ ወደ ፊት ስለ ሽልማቱ አያመነታም።

ከአሁን በፊትም ተሰጥቶ የተነጠቀ ሽልማት የለም ሲል አረጋግጧል።

በ2019 በተለያዩ የኖቤል ሽልማት በእያንዳንዱ ዘርፍ የኖቤል አሸናፊ የሚሆኑ ግለሰቦች እያንዳንዳቸው ከ900 ሺህ ዶላር በላይ ሽልማት የሚያገኙ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም