አትሌት ሰለሞን ባረጋ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች አትሌቲከስ ውድድር ከሚጠበቁ አትሌቶች አንዱ ሆኗል

348
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2010 ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ በፊንላንድ ቴምፔሬ ከሐምሌ 3 እስከ 8 ቀን 2010 ዓ.ም በሚካሄደው 17ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች አትሌቲከስ ውድድር ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል በዋንኛነት ተጠቃሽ ሆኗል። የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በውድድሩ ላይ የአትሌቲክስ አፍቃሪው ሊመለከታቸው ይገባቸዋል ያላቸውን 10 አትሌቶች ስም ዝርዝር ትናንት ይፋ ያደረገ ሲሆን አትሌት ሰለሞን ባረጋ አንዱ ሆኗል። አትሌት ሰለሞን በታዳጊ እድሜው ባሳየው አስደናቂ ብቃት በአጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ ከሚባሉ ሯጮች ተርታ ራሱን ማሰለፍ እንደቻለ ተገልጿል። ከሁለት ዓመት በፊት 16ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር በፖላንድ ባይዶዥ ከተማ በሚካሄድበት ወቅት አትሌቱ በ5ሺህ ሜትር ውድድር አሸናፊ ሲሆን ያን ያህል ታዋቂ እንዳልነበረ የማህበሩ ዘገባ ያመለክታል። ባለፉት ሁለት ዓመታት የ18 ዓመቱ አትሌት ሰለሞን ባሳየው ብቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሙን ከፍ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነት ማግኘት ችሏል። በፊንላንድ በሚካሄደው ውድድር በ5 ሺህ ሜትር ሩጫ የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት እንደተሰጠውና ውድድሩን ማሸነፍ ከቻለ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር ታሪክ በተከታታይ በ5 ሺህ ሜትር ያሸነፈ የመጀመሪያው አትሌት እንደሚሆን ተጠቅሷል። ባለፈው ዓመት በስዊዘርላንድ ሉዛን በተካሄደ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ በ5ሺህ ሜትር 12 ደቂቃ 55 ሴኮንድ 58 ማይክሮ ሴኮንድ የገባበት ጊዜ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቱ ሆኖ ተመዝግቦለታል። በዘንድሮው ዓመት አትሌት ሰለሞን ከመካከለኛና ረጅም ርቀት የመም ውድድሮች ይልቅ በዓለም አቀፍ የአገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ ትኩረት አድርጎ በመወዳደር ስኬታማ ጊዜ እንዳሳለፈ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር አስታውቋል። አትሌት ሰለሞን ባረጋ ለፊንላንዱ ውድድር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዳደረገና ከሁለት ዓመት በፊት ያገኘውን ውጤት ለማስጠበቅ እንደሚሮጥ ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል። ጃማይካዊው የ400 ሜትር ሯጭ ክረስቶፈር ቴይለር፣ ደቡብ አፍሪካዊው የ400 ሜትር መሰናክል ሯጭ ሶካዋክሀና ዛዚኒ፣ ስዊዲናዊው የምርኩዝ ዘላይ አርማንድ ዱፕላንቲስ፣ የኩባው የስሉዝ ዘላይ ጆርዳን ዲያዝ በፊንላንዱ ውድድር ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል ናቸው። አሜሪካዊቷ የ800 ሜትር ሯጭ ሳማንታ ዋትሰን፣ ኬንያዊቷ የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ተወዳዳሪ ሴሊፓይን ቼፕሶል፣ ስዊዲናዊቷ የምርኩዝ ዘላይ ሊሳ ጉናርሰን፣ አሜሪካዊቷ የርዝመት ዘላይ ታራ ዴቪስና ሞልዶቫዊቷ የዲስከስ ወርዋሪ አሌክሳንድራ ኤሚሊያኖቭ ሌሎች በውድድሩ የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው። ኢትዮጵያም በፊንላዱ ውድድር ከ400 ሜትር ጀምሮ እስከ 10 ሺህ ሜትር ባሉ ርቀቶችና በእርምጃ ውድድርና በመሰናክል ውድድሮች ትካፈላለች። በውድድሩ ላይም 29 አትሌቶች ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም