የሰራዊቱ ግዳጅ አፈጻጸም ውጤታማና በስነ ምግባር የተቃኘ መሆኑ ተወዳዳሪ አድርጎታል

121

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ግዳጅ አፈጻጸም ውጤታማና በስነ ምግባር የተቃኘ መሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቱ እንዲጨምር ማድረጉ ተገለጸ። 

በሠላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት  መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ስምሪት ያሰለጠናቸውን 10ኛና 11ኛ ዙር ሠላም አስከባሪ ሻለቆችን አስመርቋል።

የሰራዊት አባላቱ የቅድመ ስምሪት ስልጠና ለ3 ወራት የወሰዱ ሲሆን ግዳጅ መፈጸም የሚያስችላቸውን የተኩስ፣ ወታደራዊ ሰልፍና ሌሎችም ስልጠናዎችን ወስደዋል።

በዚሁ መሰረት ተመራቂዎች በሶማሊያና አብዬ ስምሪት የሚያደርጉ ሲሆን የአብዬ 24ኛ ቦርደር ሰኪዩሩቲ ሻለቃ፣ የሶማሊያ አሚሶም ዘማች ሻለቃና የአብዬ ልዩ ልዩ ክፍል ዘማች ሬጅመንት ሻምበል ናቸው።  

በመከላከያ ሚኒስቴር የሠላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሌተናንት ጀኔራል ደስታ አብቼ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በቀጣናው ያለውን ሠላም ማረጋገጥ ለልማትና ለእድገት መሰረት መሆኑን በመገንዘብ የኢትዮጵያ መንግሥት የበከሉን እየተወጣ ነው።

ይህንንም መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሚሰጠውን ግዳጅ በአግባቡ በመፈጸም በአህጉሩ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።   

''ሰራዊቱ በሚያከናውናቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ብቃትና ባለው መልካም ሥነ ምግባር ተወዳዳሪና ተመራጭ እየሆነ መጥቷል'' ብለዋል።

''ለሰራዊቱ ተቀባይነት መጨመር መንስኤው መንግሥት የተከተለው ትክክለኛ ፖሊሲ ነው'' ያሉት ሌተናንት ጀኔራል ደስታ፤ በሠላም ማስከበር የሰራዊቱን ዝናና ተቀባይነት ለማስቀጠል ጠንካራ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።  

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ ማዕከሉ ለሠላም ማስከበር ተልዕኮ ሰልጥኖ የተሰማራ ኃይል ከተልዕኮ መልስ የድህረ ስምሪት ስልጠና ወስደው ለአገር ውስጥ ቀጣይ ግዳጅ ዝግጁ የማድረግ ተግባራትን አጠናክሮ እያከናወነ ይገኛል።

የዚህ ዙር ሰልጣኞች የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) በመላው ዓለም ጫና እየፈጠረበት ባለበት ወቅት በመሆኑ ድርብ ግዳጅ እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ''ተመራቂ ሻለቆች በስምሪት ቦታ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል'' ሲሉ አስገንዝበዋል።

የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ዳኜ በላይ በበኩላቸው ተመራቂዎች የወሰዱትን ስልጠና በአግባቡ በመተግበር እንደተለመደው ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

በቀጣይ የሚሰማራውን ኃይል የሚመሩት 5ኛ ሞተራይዝድ ኪስማዩ ሠላም ማስከበር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ገብረመድህን ገብረመስቀል ሰራዊቱ በስነ ልቦናም ሆነ በወታደራዊ ብቃት የሚሰጠውን ግዳጅ መወጣት የሚችልበት አቋም ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

የሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሌተናንት ጀኔራል ደስታ አብቼ ከሌሎች ከፍተኛ መኮንኖች ጋር በመሆን በማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ የተሰሩ ማስፋፊያዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም